6 minutes reading time (1198 words)
Featured 

ከ56ኛዉ የኢትዮጲያ ሕክምና ማህበር አመታዊ ጉባኤ ምን እንጠብቅ?

Untitled

ሀኪሞች ዶት ኮም የኢትዮጲያ ሕክምና ማህበር ፕሬዝዳንት ዶ/ር ገመቺስ ማሞ ጋር በዚህ ርእሰ ጉዳይ ቃለምልልስ አድርገጓል፡፡ ውይይቱን ዶ/ር ሳሙኤል ጌትነት እንደሚከተለው አዘጋጅቶ አቅርቦልናል፣ ተከታተሉት፡፡

ሀኪሞች፡- ዶ/ር ገመቺስ በመጀመሪያ ለቃለ መጠይቁ ፍቃደኛ ስለሆኑ እናመሰግናለን፡፡ በዘንድሮው አመታዊ ጉባኤ ምን እንጠብቅ?

ዶ/ር ገመቺስ፡- ከየካቲት 13-15 በሚደረገው ዓመታዊ ጉባኤ ልክ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው የፓናል ዲስከሽን ይኖረናል፡፡ የውይይቱ መሪ ቃልም "ወጣት ሀኪሞችን ማብቃትና የጤና ስርዓቱን ማጎልበት" የሚል ነው፡፡ የተመረጠበት አንደኛው ምክንያት፣ በአገራችንበአሁኑ ጊዜየሚገኙት ሀኪሞች በአብዛኛው ወጣት ሀኪሞች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ወጣት ሀኪሞች ስራ የማግኘት ዕድሉ እየጠበበ እንደመጣ ይታወቃል፡፡ከዚህ ቀደም በህክምና ሙያ ለሚመረቅ የስራ እድል ጥያቄ ውስጥ የሚገባ አልነበረም፡፡ በቅርብ ጊዜ የተደረገው የወጣት ሀኪሞችጥያቄ፣ የህልውና ጥያቄ፣ ይሔ ነበር፡፡ "ስለዚህ ምንድነው ማድረግ የምንችለው ወይንም ወጣቱን በምንድነው ማብቃት የምንችለው?" በሚል ሀሳብ የሚካሄድ ውይይት ይኖረናል፡፡ ከመፍትሄዎቹም አንዱ ስራ ፈጠራን እና የመሪነት ክህሎትን ማሳደግ ላይ ማተኮር ላይ ይመለከታል፡፡ ወጣት ሀኪሞች ስራ ፈላጊ ብቻ ሳይሆን ስራ ፈጣሪ መሆን መቻል አለባቸው፡፡

የመሪነት ክህሎት የሚያስፈልግበት ምክንያት፤ የህክምና ስራ የቡድን ስራ እንደመሆኑ መጠን ሀኪም መሪ መሆን አለበት፡፡ ነገርግን ብዙውን ጊዜ ሀኪሞቻችን በህክምና ስራው ላይ እንጂ በመምራቱ ላይ ሲሳተፉ አናይም፤ በዚህም ምክንያት ሀኪሙም ህክምናውም ተጎድቷል የሚል አመለካከት አለን፡፡ ስለዚህ ሀኪሞቻችንን በአመራር ልምድ/ክህሎት/ ማብቃት የሚለውን እንደ አንድ መሪ ቃል ይዘነዋል፡፡

ሌላው ጉዳይ የጤና ዘርፉ ኋላቀር ነው ማለት ይቻላል፤ በተለይ ደግሞ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ዙሪያ፡፡ በኢትዮጲያ ውስጥ ዘመኑን የጠበቀ የኮምፒውተር ሲስተምን ወይንም ዳታቤዝን የሚጠቀሙ የጤና ድርጅቶች በቁጥር አናሳ ናቸው፡፡ ዘመናዊ የኢንፎርሜሽን ሲስተም የጤና ዘርፉን እንደሚያጎለብተው ግልጽ በመሆኑ፣የዘመኑን ቴክኖሎጂ በመጠቀም መጪውን ጊዜ ለመዋጀት በሀገር ውስጥና ከሀገር ውጪ ያለውን ልምድ የምንለዋወጥበት መድረክ ይኖረናል፡፡

ከዚህ ባለፈ ከዚህ በፊት እንደሚደረገው የተመረጡ የሪሰርች ፔፐሮች በኦራልና ፐፖስተር ፕረዘንቴሽን የሚቀርቡ ይሆናል፤ የተወሰኑ ሳይድ ሴሽኖች፣ ስቴት ኦፍ ዘ አርት ሌክቸር ይኖረናል፡፡ ሌላው በማህበሩ አባልት እና በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው የተመረጡ፣ አርአያ ሊሆኑ የሚችሉ ጁኒየርና ሲንየር ሀኪሞች ዕውቅና የሚያገኙበት የሜሪት አዋርድ ፕሮግራም ይኖራል፡፡

ሀኪሞች ፡- ከዚህ ጋር ተያይዞ ከተለመደው የተለየ ነገር ምን ሊኖር ይችላል?ዶ/ር ገመቺስ፡- ምናልባት የሜሪት አዋርድ ተሸላሚዎችን በመለየት ዙሪያ ህብረተሰቡ የሚሳተፍበት ሁኔታ ለማመቻቸት መጠይቆች የተላኩ ሲሆን የተለያዩ ጥቆማዎችን ለመቀበል ዝግጅት ተደጓል፡፡ የሚቻልም ከሆነ የተሸላሚውን ህይወት በሚቀይር ሁኔታ ሽልማቱን መስጠት እንፈልጋለን፡፡ ከዚህ በፊት የነበረን ትልቁ ተግዳሮት ለእንደነዚህ አይነት እውቅናዎች ድጋፍ የሚያደርጉ ድርጅቶችን ማጣት ነበር፣ አሁን ግን ያገኘን ይመስለናል፤ እየሰራንበትም ነው፡፡

ላለፉት አራት አመታት እንደተለመደው፣ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ሩጫ የሚካሄድ ይሆናል፣ ነገርግን ጊዜውን አስመልክቶ፣ ምናልባትም ከአፍሪካ ህብረት ስብሰባ ጋር የሚቀራረብ ስለሚሆን ፍቃድ ለማግኘት ከሚመለከተው አካል ውሳኔውን በመጠበቅ ላይ እንገኛለን፡፡ ከዚህም ሌላ ለአምስተኛ ጊዜ የሚኖረን ፕሮግራም ደግሞ እራት ግብዣ ነው፣ የዘንድሮ ስብሰባ አጋር የኢትዮጲያን አየር መንገድ በመሆኑ ስብሰባው የሚካሄደውም በስካይላይት ሆቴል ይሆናል፡፡ ይህ ለ56ኛ ጊዜ የሚካሄደው የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር-ኢቲ ጉባኤ የሚሳካ ከሆነ ከኢትዮጲያን አየር መንገድ ጋር የሚኖረን ፓርትነርሺፕ ቀጣይነት እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡

ሀኪሞች፡- ለምን ኢትዮጲያ ህክምና ማህበር የኢትዮጲያን አየር መንገድን አጋርነት ፈለገ?

ዶ/ር ገመቺስ፡- ሜዲካል ቱሪዝም በኢትዮጲያ ውስጥ እንዲስፋፋ እንፈልጋለን፡፡ሜዲካል ቱሪዝም የሁለት አቅጣጫ መንገድ ነው፣ በሽተኛን መላክ ብቻ ሳይሆን በሽተኛን መቀበልም ይጨምራል፡፡ በዚህም እውቀትና ልምድ መስጠትና መቀበል አለብን የሚል የቆየ አቋም አለን፡፡ በሀገራችን የሚሰጠው የህክምና አገልግሎት በአቅራቢያችን ከሚገኙ ጎረቤት ሀገራት የተሻለ እንጂ ያነሰ እንዳልሆነ እናምናለን፡፡ የጤናው ሰርቪስ በተለይም ደግሞ የግሉ የህክምና ዘርፍ ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ መቱዋል፣ ይህንን ማስተዋወቁ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

ከዚህ በተረፈ ከውጪ በሚመጡ የሆስፒታል ባለሙያዎች ያላቸውን እውቀትና ክህሎት የሚያስተላልፉበትን መንገድ መፍጠር ይኖርብናል፡፡ ይህንን የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ጉባኤ ከዛሬ 3-4 ዓመት በፊት እንደጀመርነው አለም-አቀፍ ጉባኤ ብናደርገው፤ ውጪ በዱባይ ወይንም በሻንጋይ ወይንም በጀርመን እንዳለው የህክምና አውደርዕይ ቀናቶች ዓይነት ልናደርገው እንችላለን፡፡ በትንሹም በምስራቅ አፍሪካም ደረጃ ከፍ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ለዚህም ዘንድሮ መሰረቱን መጣል ብንችል ወደፊት ቀጣይነት ይኖረዋል የሚል እምነት አለን፡፡ በተለያዩ አገሮች የተሰሩ ጥናቶች አሁንም ኢ.ኤም.ጄ ላይ እንደሚታተሙት ፣በተለይም ደግሞ ጥራታቸውና ተቀባይነታቸው ከፍ ያለ ውጪ የተሰሩ ጥናቶች ብናገኝና በእኛ መድረክ ላይ የሚቀርቡበትን መንገድ ብንፈጥር ለኢትዮጲያ ህክምና ማህበርና ለሀገሪቱ እንደ የገቢ ምንጭ እና ክብር አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ለዚህም ነው ከኢትዮጲያ አየር መንገድ ጋር ለማያያዝ ያስፈለገን፡፡ 


ሀኪሞች፡-ዘንድሮ የህክምና ማህበሩ አዳዲስ አመራሮችን ይመርጣል ተብሎ ይጠበቃል፤ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላሉ?

ዶ/ር ገመቺስ፡- የዛሬ 5 ዓመት የተመረጠው ኮሚቴ ሁለት ተርሙን ጨርሶ የሚያስረክብበት ጊዜ ነው፡፡ ካሉት 6 የኮሚቴ አባላት ውስጥ ከአንዱ በስተቀር ሁሉም አስረክቦ ለአዲስ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አስረክቦ ይለቃል፡፡ ነገርግን መመረጥ አንደሚታሰበው ቀላል አይደለም፡፡ ምክንያቱም የህክምና ማህበረሰቡ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ‹‹ተዳክሟል›› የሚል አስተያየት ሲሰጥ ቢሰማም ወደትግበራ ሲመጣ የባለሙያው ተሳትፎ ግን ዝቅተኛ ነው፡፡መመረጥ ብቻ ሳይሆን መምረጥም ችግር ነው፣ ከዚህ በፊት እንዳየነው፡፡ በተለይም ወጣቱ ትውልድ ከእኛ በፊት የነበሩት ታላላቆች ያስረከቡትን፣ እኛም ተቀብለን ያቆየነውን ማህበር ወደፊት ሊያሻግረው ይገባል፡፡ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር አቅሙ በጣም ትልቅ ነው፣ ሁሉም ሰው የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር እንዲኖርና እንዲያድግ ይፈልጋል፡፡ ነገርግን ከፍላጎት ባለፈ መስራት ደግሞ ሌላ ነገር ነው፡፡ እንግዲህ የእኛም እምነት የኢትዮጲያ ህክምና ማህበርን ማህበር የሚያቆዩ ብቻ ሳይሆን የሚያሳድጉም የስራ አስፈጻሚዎች የሚመረጡበት ዘመን እንደሚሆን ተስፋ እናደርጋለን፡፡

ይሄን በተመለከተም በሚዲያችን ላይ ያሳወቅን ቢሆንም የሚካድበትን አግባብ በስብሰባው ግዜ የምናየው ይሆናል፡፡ እንደእኔ እምነት ወጣቱ መምጣትና ማህበሬ ነው ብሎ መሳተፍ አለበት፡፡በስፔሻሊቲ ደረጃ የተቋቋሙና በስፔሻሊቲው ጉዳይ /ሙያው/ ላይ ብቻ የሚያተኩሩ እንዲሁም በክልል ደረጃ የተቋቋሙ የተለያዩ ማህበራት አሉ፡፡ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ግን ዘር፣ ቦታን፣ጾታንና ቋንቋን ሳይለይ አጠቃላይ ሀኪሞችን የያዘ ማህበር ነው፡እኛን አንድ የሚያደርገን በመጀመሪያ ላይ የገባነው ሂፖክራቲክ ቃለ-መሀላ ነው፡፡ለሁሉም ሀኪም ጥቅም በጋራ የቆመው የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር፣ እንደ እናት ማህበር፣ የበለጠ መጠናከር አለበት፡፡ ሌሎቹም መጠናከር አለባቸው፡፡

ታዲያ ‹‹ይሄ እንዴት ነው መጠናከር የሚችለው ? በቅርቡስ ሚነሱት ጥያቁዎች ምንድናቸው? ጥያቄዎቹስ እንዴት ምላሽ ማግኘት ይችላሉ ?›› በሚሉት ጉዳዮች ላይ በቅርብ ያለው ወጣቱ ስለሆነ ወጣቱ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚኖርበት አሳስባለሁ፡፡ ነገርግን ወጣቱ ብቻውን የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ይዞ የመጣውን እሴት ይዞ ይሻገራል የሚል እምነት የለኝም፤ ምክንያቱም ማህበራችን መጀመሪያ ይዞት የተነሳው አላማ የሳይንቲፊክ ማህበር እንዲሆን እና በህክምናው ላይ ምርምርና ክርክር የሚደረግበት እንጂ የመብት ጉዳይ የሚነሳበት ማህበር እንዳልነበረ ይታወሳል፡፡ በዚያን ጊዜ ይቀርቡ የነበሩት የምርምር ወረቀቶች ለየት ያሉ እንደሆኑና፤ ይህንን መለያውንና ክብሩን ይዞ እንዲሻገር በእድሜ እና በልምድ ጠንከር ያሉ ሰዎች ያስፈልጉናል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያለበለዚያ ወጣቱ ያለውን ነገር ብቻ ይዤ ልሂድ የሚል ከሆነ ታሪኩን ያጣ ማህበር ነው ሚሆነው፡፡ በአሁኑ ወጣት ዘንድ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር እንዳለ እንኩዋን የማያውቅ ሀኪም ያጋጥመናል፡፡ ስለዚህ ወጣቱን ይዞ መሄድ ስለሚያስፈልግ እንደእኔ ሁለቱንም ያቀፈ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ቢቋቋም መልካም ነው፡፡

ነገርግን ከሁሉም በላይ፣ የሚመረጡት መሪዎች በፍላጎት የሚመሩ መሆን አለባቸው፡፡ ሰዎች ‹‹ለኢትዮጲያ ማህበር መስራት እፈልጋለሁ፣ መጮህ እፈልጋለሁ›› ብለው እንጂ ተገፍተው፣ተለምነው መምጣት የለባቸውም፣ያ ያመጣውን ችግር እናውቃለን፡፡ ቢቻልም በፉክክር ተከራክረው ቢመረጡ ደስ ይለኛል፡፡ ነገርግን ይህ የጠቅላላ ጉባኤው ውሳኔ ይሆናል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በኛ የስራ ዘመን ወቅት ያጋጠሙንን ተግዳሮቶች እና ስኬቶች በስብሰባው ወቅት በሰፊው እናቀርባለን፡፡

ሀኪሞች፡- በመጨረሻም ለሀኪሞች ሊያስተላልፉ የሚፈልጉትን መልእክት ካለ ?

ዶ/ር ገመቺስ፡- የሀኪሞቻችን ችግር፤አዲስ ነገር አይደለም፣ በኛ ጊዜም ነበር፡፡ ደግሞም አዲስ ችግርም አለ፡፡ በተለይም በወጣቱ ላይ ያለው ትልቁ ፈተና ተስፋ ማጣት ነው፤ እኔ በተማርኩ ሰዓት እና ከእኔ በሁዋላም በመጡ ሀኪሞች ዘንድ ስንማር ስራ እንደምናገኝ አምነን ነው፡፡ አሁን የሚማር ሀኪም ግን ስራ ለማግኘቱ እርግጠኛ አለመሆኑ፣ በዚህ ሰዓት ስራ አጥተው የተቀመጡ ሀኪሞች በቂ ምስክር ናቸው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም የሚያሳስበው፤ እውነት ለመናገር የህክምና ትምህርት ጥራቱ እያነሰ ያለበት ሁኔታ ነው ያለው፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ለብዛት ትልቅ ትኩረት እየሰጠን ስላለ ነው፡፡ አንዳንድ የህክምና ትምህርት ቤቶች ስፔሻሊቲ በሌላቸው ጠቅላላ ሀኪሞች እያስተማሩ ነው፤ ይሄ ደግሞ ሊያሳስበን ይገባል፡፡ በዚሁ ሁኔታ የሚመረቁ ሀኪሞች ነገ ጠዋት እኛን እንደሚያክሙ ማሰብ አለብን፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ ትልቁ በደል በባለሙያው ምክንያት ሙያው መሰደቡ ነው፡፡ ሁላችንም የህክምና ጥራት እንዲኖር በያለንበት ቦታ ላይ ጥረት ማድረግ አለብን፡፡ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር የሁላችንም ነው፤ ሁላችንንም የሚያሰባስበን ይህ ማህበር ነው፤ ከበረታንና ከጠነከርን ልክ እንደምንኮራባቸውና እንደምንናፍቃቸው የውጪ የህክምና ማህበሮች ማህበራችንን ትልቅ ልናደርገው እንችላለን፡፡ ካልሆነ እንዲሁ እየተገንገታገትን ይቀጥላል፡፡ ጎበዝ ጠንካራ የሆነ የስራ አስፈጻሚ ካገኘ የተወሰነ ይራመዳል፣ እንዲሁ ደካማ የስራ አስፈጻሚ ካለ የተወሰነ ወደኋላ ይቀራል ነገር ግን የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር መቀጠሉ አይቀርም፣ ምክንያቱም ከእኛም በፊት ነበር ከእኛም በኋላ መቀጠሉ አይቀርም፣ ነገርግን መኖሩ ብቻ በቂ አይደለም፣ ስለዚህ የኢትዮጲያ ህክምና ማህበር ጠንክሮ እንዲሄድ ሀኪሞች በሙሉ በጋራ መስራት አለባቸው ለማለት እፈልጋለሁ፡፡

ሀኪሞች፡- ለሰጡን ጊዜ እና አስተያየት በሀኪሞች ዶት ኮም ተከታታዮች ስም እናመሰግናለን፡፡ 

ብሔራዊ የሚጥል ሕመም ሳምንት በኢትዮጵያ ለ5ኛ ጊዜ ይከበራል::
አጠቃላይ ገበያ ላይ የሚውሉ የህክምና መስጫ መሳሪያዎች ለመርመር የላብራቶሪ መሳ...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Tuesday, 16 August 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/