11 minutes reading time (2242 words)

"የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገናን የቀን ተቀን አገልግሎት እንዲሆን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡"

"የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገናን የቀን ተቀን አገልግሎት እንዲሆን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡"

ሀኪሞች ዶት ኮም የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ከሆነው ከዶ/ር ያየህይራድ መኮንን ጋር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ቃለ ምልልሱን ሎዛ አድማሱ እንደሚከተለው አዘጋጅታ አቅርባልናለች፣ ተከታተሉት፡፡ 

 ሀኪሞች:- ራስህን አስተዋውቀን፡፡

ስሜ ዶክተር ያየህይራድ መኮንን ይባላል፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪዬን በ ሜዲስን (ሰባት አመት) እና ስፔሻሊቲ በ ጠቅላላ ቀዶ ህክምና (አራት አመት)፣ በአጠቃላይ 11 አመት ጅማ ዩኒቨርሲቲ ነበርሁ፡፡ ከ 2012-2017 G.C. ጠቅላላ የልብ ቀዶ ህክምና ( General Cardiac Surgery)ን እስራኤል ሀገር አጥንቻለሁ ፡፡ ከ 2017-2019 ለ አንድ አመት ተኩል የ ህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና(Pediatric Cardiac Surgery Fellowship)ን በአውስትራሊያ ስከታተል ነበር፡፡ ከሰባት አመት በኋላ፣ May 2019 ወደ ኢትዮጲያ ተመልሼ በመምጣት በቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ሚሊኒየም ህክምናኮሌጅ ተቀጥሬ፣ በ የልብ ማእከል በኢትዮጵያ (Cardiac Center-Ethiopia) እየሰራሁ እገኛለሁ፡፡ ባለትዳርና የሁለት ልጆች አባት ስሆን፣ እኔም ቤተሰቤም ኑሯችን በአዲስ አበባ ነው፡፡

ሀኪሞች:- ተቀጣሪነትህ በቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ሆኖ እንዴት በ ልብ ህክምና ማእከል ልትሰራ ቻልህ?

የልብ ቀዶ ጥገና ኢትዮጵያ ውስጥ ከልብ ማእከል ውጪ በስፋት ስለማይሰራ፤እና ህክምና በተፈጥሮው የቡድን ስራ በመሆኑ በልብ ህክምና ዙሪያ ከሰለጠኑ ባለሙያዎች በጋራ እየሰራን እንገኛለን፡፡ ከልብ ቀዶ ህክምና ሀኪም በተጨማሪ ሌሎች ስፔሻላይዝድ ያደረጉ ባለሙያዎች ማለትም፣ Cardiologist, Cardiac Anesthesiologist , Intensivist, Perfusionist, ICU Doctor, ICU Nurse, Scrub Nurse አንድ ላይ መስራት አለባቸው፡፡ ሙያው አዲስ እንደመሆኑ መጠን፤ ሌሎች ማዕከሎች እስኪከፈቱ በዚህ ማዕከል እየሰራን አና ሌሎች ሐኪሞችንም እያሰለጠንን እንቆያለን፡፡

በልብ ማእከሉ በኩል ከቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ ጋር በተደረገ ስምምነት የቅዱስ ጳውሎስ ባለሙያዎች (Intensivist, Perfusionist) አብረን ከልብ ማዕከል ባለሙያዎች ጋር አብረን እዚህ እንድንሰራ ተደረገ፡፡ የቅዱስ ጳውሎስ ሆሰፒታል ሚሊኒየም ህክምና ኮሌጅ የልብ ማዕከል ዝግጁ ሲሆን ወደዛ ተዘዋውረን የምንሰራ ይሆናል፡፡ 


 ሀኪሞች:- በህጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ስፔሻላይዝ እንድታደርግ ምን አነሳሳህ?

እርግጠኛ ሆኜ ይሄ ነው ማለት አልችልም፡፡ ግን ጅማ እያለን ይመስለኛል፡፡ የ Clinical Year ተማሪ እያለን የህጻናት ህክምና ላይ መስራት እንደምፈልግ አስብ ነበር፡፡ ኢንተርንሺፕ እያልሽ ምን እንደምትፈልጊ፣ ምን ላይ ጥሩ ላይ እንደሆንሽ እያወቅሽ ትሄጃለሽ፡፡ ኢንተርንሺፕ ስጨርስ ቀዶ ጥገና ላይ ፍላጎት እንዳለኝ ተረዳሁ፡፡ 


ፔዲያትሪክስ ሮቴሽን እያለን ከመምህራኖቻችን አንዱ የህጻናት የልብ ሀኪም የሆኑት ፕሮፌሰር አብርሀም ራውንድ ስናደርግ በተደጋገሚ የልብ ቀዶ ጥገና ባለመኖሩ ህይወታቸውን ስለሚያጡ ህጻናት ይነግሩን ነበር ፡፡ እዚያ በተደጋጋሚ አልጋ የሚይዙ ታካሚዎች ነበሩ፡፡ Chronic Heart failure, VSD with Eisenmenger's Syndrome ያላቸው ሲያኖቲክ ህጻናት ታካሚዎች እሰከዛሬ በውስጤ ቀርተዋል፡፡ እና እነሱ እነሱን ሳይ ምናልባት እኔ እዚህ ሙያ ላይ መሰማራት አለብኝ ብዬ አሰብሁ፡፡


በእስራኤል የመማር እድልን ያገኘሁት በፕሮፌሰር አብርሀም በኩል ነው ፡፡ ፕሮፌሰር አብርሀም በሳቸው ተነሳሽነት ብዙ ሰዎች የህጻናት ቀዶ ህክምና ላይ ፍላጎት እንዲያድርባቸው ብዙ ጥረት አድርገዋል፡፡ መመስገን የሚገባቸው ትልቅ ሰው ናቸው፡፡


"ህክምና በተፈጥሮው የቡድን ስራ ነው፡፡......በሙያዎች መሀከል ትብብር እና ተጠያቂነት ያስፈልጋል፡፡"


 ሀኪሞች:- የእስራኤል ቆይታህ እንዴት ነበር?

ይሄ እድል ልክ ጠቅላላ ቀዶ ህክምና ሬዝደንሲ እንደጨረስሁ የተገኘ ነበር እና ለመሄድ አወላውዬ ነበር፡፡ ሬዚደንሲ የጀመርኩት ወዲያው የህክምና ትምህርት እንደጨረስኩ ስለነበረ የተወሰነ ጊዜ ከትምህርት ማረፍ ፈልጌ ነበር፡፡ ለብቻዬ ሆኜ ችሎታዎቼን እና በትክክል ምን አይነት ሰው እንደሆንሁ ለመረዳት ፈልጌ ነበር፡፡ እንደሀኪም ለብቻሽ ሆነሽ፣ ውሳኔ እያሳለፍሽ፣ ቡድን እየመራሽ፣ በራስሽ ህሙማንን እያየሽ፣ ካልሆነ እንዴት ያለ ሀኪም መሆንሽን መቼም ማወቅ አትችይም፡፡ በሙያ ብቻ ሳይሆን በማህበራዊ ህይወትም ጭምር ልታውቂያቸው የሚገቡ ነገሮች አሉ፡፡ ትዳር መመስረት ልታስቢ ትችያለሽ፡፡

ግን ደግሞ በወጣትነቴ ቶሎ ተምሬ ብጨርስ እና ቶሎ ብመጣ ብዙ ታካሚዎችን መርዳት እችላለሁም ብዬ አሰብሁ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ያው እስራኤል ስሄድ መካከለኛው ምስራቅ ነውና ብዙ የሚያሳስቡ ነገሮች አሉ፡፡ ብቻ መጨረሻ ሄድሁ፡፡ እስራኤል ግን የገጠመኝ ነገር በጣም ጥሩ ነበር፡፡ ትምህርታችንን ስፖንሰር ያደረገን አለም-ዐቀፍ የቻሪቲ ድርጅት ስለነበር ከሚታከሙት ታካሚዎች 40 ፐርሰንት የሚመጡት ከአፍሪካ ነበር፡፡ በጥሩ የህክምና ማዕከል የአፍሪካ ታማሚዎች እንዴት ማከም እንደሚቻል መማሩ ትልቅ እድል ነበር፡፡ ከዚህ በፊት የልብ ህክምና ትምህርት ስላልወሰድኩ፣ ከአምስቱ አመታት የመጀመርያውን Cardiac ICU, Cardiac Anesthesia እና Cardiology ነው ስማር የነበረው፡፡ የአራቱ አመት ስልጠና Intensive እና ቀዶ ጥገና ላይ ተኮረ ነበር፡፡ እሰራኤል ውስጥ በጣም ብዙ ኢትዮጲያውያን አሉ፣ ከፈለግሽ እንጀራም አማርኛም አለ፡፡ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መጥተው የሚሰለጥኑ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ ቋንቋውንም በቶሎ ነው የተማርኩት፡፡ ትዳር የመሰረትሁትም፣ የመጀመሪያ ልጄን የወለድሁትም እስራኤል ነው፡፡

ሀኪሞች:- ሜልቦርን ቆይታህ እንዴት ነበር? የእስራኤሉ ስልጠና ቀጣይ ክፍል ነው ?

አምስቱን አመት ከጨረስሁ በኋላ የህጻናት የልብ ቀዶ ህክምና ትምህርት ማግኘት ነበረብኝ፡፡ እስራኤል ሳለሁ የማንሰራቸው ነገሮች ነበሩ፡፡ ለምሳሌ የልብ ንቅለተከላ (Cardiac Transplant) አንሰራም ነበር፡፡ አብዛኞቹ ታካሚዎቻችን ከአፍሪካ ስለነበሩ፤ የጨቅላ ህጻናት ቀዶ ህክምና (Neonatal Surgery) የሚሰራባቸው አጋጣሚዎች አልነበሩም፡፡ ስልጠናውን ለማጠናቀቅ እነዚህን ነገሮች መማር እፈልግ ነበር፡፡በ Pediatrics Cardiac Surgery Fellowship ከታወቁ ጥቂት ትላልቅ ሆስፒታሎች መካከል የ Melbourne Royal Children Hospital አንዱ ነው፡፡ ሆስፒታሉ በመላው አውስትራሊያ ብቸኛው የህጻናት የልብ ንቅለተከላ ማዕከል ነበር፡፡ ከዚ በፊት ሆስፒታሉን የማየትም አጋጣሚ ስለነበረኝለፌሎውሺፕ አመልክቼ ነበር፡፡ ብዙ ሰው ስለሚያመለክት እድሉን ለማግኘት ሁለት አመት መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ እናም ተቀበሉኝ፡፡ እስራኤል ሰኔ ላይ ጨርሼ እዚያ ነሀሴ ነው የጀመርሁት፡፡ አንድ አመት ከስምንት ወር ከቆየሁ በኋላ ወደዚህ መጣሁ፡፡ሀኪሞች:- ወደ ኢትዮጲያ እንዴት ተመለስክ?

በመጀመሪያ ደረጃ እዚህ መምጣት በራሱ ፈተና ነበር፡፡ ምክንያቱም እዚያ ሁሉ ቦታ ስትሄጂና መጀመሪያ ሰዎች ስታገኚ፣ ያው ስምሽን እና ስለመጣሽበት ቦታ ከጠየቁሽ በኋላ፣ ኢትዮጲያ ውስጥ የልብ ቀዶ ህክምና በደንብ ይሰራል ወይ? ስንት የቀዶ ህክምና ባለሙያ አለ? ስንት የልብ ህክምና ማዕከል አለ? ብለው ነው የሚጠይቁሽ፡፡ እና ሀገርሽ ውስጥ ካሉት ጥቂት ባለሙያዎች አንዱ ሆነሽ ሌላ ቦታ ራስሽን ማግኘት የሆነ የሚያስገምት ነገር አለው፡፡ ሰዎች ሊገምቱሽ ፈልገው ባይጠይቁሽ እንኳን እንደዚያ ይሰማሻል፡፡ ስለዚህ መምጣት ፈለግኩ፡፡ ምክንያቱም ለአውስትራሊያ ወይም ለእስራኤል እኔ ከውቅያኖስ አንድ ጭልፋ እንደማለት ነኝ፡፡ እዚህ የመጣሁት ኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ መስራት እችላለሁ ብዬ ነው፡፡ በርግጥ ብዙ አማራጮች ነበሩ፡፡ ሌላ ቦታ የመኖር፤ ልጆቼን ሌላ ቦታ የማሳደግ፤ የተሻለ ትምህርት ቤት ማስተማር… ግን እኔን ያሳደገችኝ ኢትዮጲያ ለልጆቼ ታንሳለች ብዬ አላስብም፡፡ እኔን እዚህ ያደረሰች ኢትዮጲያ ፤ልጆቼንም የፈለጉበት ማድረስ ትችላለች ብዬ አምኜ ነው የመጣሁት፡፡

ሀኪሞች:- የዉጭው አለምን ህክምና አሰጣጥ ከሀገራችንን ጋር ስታነጻጽረው፣ ምን ተሞክሮ መውሰድ ይቻላል?

ዉጭ የሄድሁ ጊዜ በጣም ገርሞኝ የነበረው ነገር ፣ የስራ ስነምግባር (Work Ethic) ጉዳይ ነበር፡፡ እነኚህ ነገሮች እኛ ጋር ትንሽ አልተለመዱም፡፡ ለምሳሌ በሰዐት ከስራ መውጣት ወይም በሰዐት ስራ መግባት፣ ሲኒየር ሲጠራ አለመምጣት፣ የመሳሰሉት ነገሮች አሉ፣ በእርግጥ እነኚህን ነገሮች ኢትዮጲያ ውስጥ ያለ ሀኪም ወዶ የሚያደርጋቸው አይመስሉኝም፡፡ የኑሮ ሁኔታው የሚገፋው ይመስለኛል፡፡ ሌላ ቦታ ደግሞ ስትሄጂ የህዝብ ሆስፒታል ውስጥ የሚያስፈልግሽን ያህል ገንዘብ ታገኛለሽ፡፡እዚያው የግል ህክምናም (Private Service) እና ሌሎች ስርአቶችም አሉ፡፡

ሌላ እዚያ ያየሁት፤ ሁሉም ባለሙያ ታካሚ የኔ ነው ብሎ ያስባል፡፡ ጅማ እያለሁኝ ታካሚው እኔ ቀዶ ጥገና ከሰራሁት የእኔ ታካሚ ነው፡፡ እዚያ ግን Nurse, Anesthetist, Cardiologist, Surgeon ሁሉም የእኔ ታካሚ ነው ይላሉ፤እና ሙሉ ሀላፊነትም ይወስዳሉ፡፡ ይሄ የእከሌ፤ ይሄ የእከሌ፤ ስራ ነው የለም፡፡ ሁሉም ሀላፊነት ይወስዳል፡፡ እኛም ሀገር ይሄ የስራ ባህል አለ ግን ብዙ መስተካከል ይፈልጋል፡፡ በተለይም በሙያዎች መሀከል ትብብር እና ተጠያቂነት ያስፈልጋል፡፡

ሌላው፣ Infection Prevention በታማኝነት ማድረግ ነው፡፡ ሰው አየኝ አላየኝ ብሎ ሳይሆን እጅሽን የምትታጠቢው አስፈላጊ መሆኑን ተረድተሸ መሆን አለበት፡፡ አሁንም ቢሆን ይሄ ነገር ኢትዮጵያ ውስጥ የማይደረገው በብዙ እቃዎች እጥረት ሊሆን ይችላል፡፡ ግን ይሄ የታካሚ ደህንነት ጉዳይ ስለሆነ ለድርድር የሚቀርብ አይደለም፣ መሻሻል አለበት፡፡

ሌላ መንግስት በህክምና ተቋማት ላይ ያለው ትኩረት ነው፡፡ ለማህበረሰቡ ደህንነት ሲባል፣ በመንግስት እና በሆስፒታሎች መሀከል መሰማማት ያስፈልጋል፡፡ የህክምና እቃዎች ሊቀርብ የሚገባው በሆስፒታሉ ፍላጎት መሰረት ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት መሆን አለበት፡፡ አሁን ለምሳሌ አውስትራሊያ ለዚያ የልብ ማዕከል ብቻ ተለይተው የሚደረጉ ነገሮች አሉ፡፡ መንገድ አሰራር ሊሆን ይችላል፣የእቃ አቅርቦት ሊሆን ይችላል:: ለሆስፒታሉ የሚያስፈልጉ የተለዩ ነገሮች መንግስትም ትኩረት አድርጎ ይሰራቸዋል፡፡ የሆስፒታል አሰራር ከመንግስት ወደ ባለሙያ ሳይሆን ከባለሙያ ወደ መንግስት መሆን አለበት፡፡ይሄን መልመድ ያለብን ይመስለኛል፡፡ ሀኪሞች:- የልብ ቀዶ ህክምና በተመለከተ ምን አይነት ተግዳሮቶች አሉ? መልካም እድሎችስ?

አንዱ ፈተና፣ በማወቅም ወይም ባለማወቅ የመንግስት አትኩሮት፤ በቀን ውስጥ በጣም ብዙ ህጻናትን ሊገድሉ ይችላሉ ተብለው የሚታሰቡ በሽታዎች እንደ ወባ፣ ኒሞንያ፣ ቲቢ፣ኤች አይ ቪ… ላይ ነው፡፡እነኚህም በጣም አስፈላጊ ቢሆኑም፤ ግን ደግሞ Congenital Heart Disease/CHD/ እና Rheumatic Heart Disease የመሳሰሉትም ላይ ትኩረት ሊሰራ ያስፈልጋል፡፡ ከ100 ህጻናት አንዱ ከ CHD ጋር ይወለዳል፡፡ ከነኚህ ደግሞ 30 ፐርሰንቱ ቀዶ ጥገና ይፈልጋሉ፡፡ ይህን በአለም አቀፍ ደረጃ ካለው አመታዊ የወሊድ ቁጥር ጋር ብታይው በአመት ወደ 8000 የሚጠጉ ህጻናት ማለት ነው፡፡ እንግዲህ እነኚህ ወደሆስፒታል የመጡትና እኛ የምናገኛቸው ናቸው፡፡ ጉዳቱን ተሸክመው ኑሯቸውን የቀጠሉትን ምልክት ያላሳዩትን ትተን ማለት ነው፡፡ ያን ያህል የስፋቱ ያህል አትኩሮት የተሰጠው አይመስለኝም፡፡ አሁን የተጀመረው ነገር ጥሩ ቢሆንም፣ ከዚህ የበለጠ ትኩረት ተሰጥቶት የሚያስፈልጉት ድጋፎች መደረግ አለባቸው፡፡ ሆስፒታሎች መሰራት አለባቸው፣ መገልገያዎችመሟላት አለባቸው፣ ለትምህርት ወደ ውጪ ብዙ ሰው መላክ አለበት፡፡ ማሰልጠን ከተቻለ እዚህ የምናሰለጥንበት መንገድ መመቻቸት አለበት፡፡ እና ይሄ ትልቅ ፈተና ነው፡፡ የታካሚ ቁጥር እና የሆስፒታሎች ዝግጁነት አይመጣጠንም፡፡

ሁለተኛው እክል፣ እዚህ ሆስፒታል ብዙ እቃዎች አሉ፡፡ ሁሉ ነገር መስራት ይቻላል፡፡ ግን አሁን ትልቁ ፈተናችን አላቂ እቃዎች ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ነገሮች ተጠቅመን የምንጥላቸው እንጂ ደጋግመን የምንጠቀማቸው አይደሉም፡፡ እነዚህ የምንጠቀማቸውን አላቂ እቃዎች ቶሎ የሚተካ እና የሚያሟላ ስራውን የሚያስሄድ ሲስተም ሊኖር ይገባል፡፡ ያ ማለት ግብአቶችን የሚቆጣጠር ሰውና ገንዘብ /Supply Management/ ያስፈልጋል፡፡ አሁን ለምሳሌ በዚህ ሳምንት (ቃለ መጠይቁ በተደረገበት ሳምንት) ቀዶ ጥገና አልሰራንም፡፡ ምክንያቱም የABG Reagent እጦት ነው፡፡ በዚያም ላይ እነኚህ ነገሮች በቀላሉ ኢትዮጲያ ውስጥ የሚገኙ ነገሮች አይደሉም፡፡ ከውጪ የሚመጡ ስለሆኑ፤ተጠቅመን ስንጨርሰ ረጅም ጊዜ መጠበቅ እንገደዳለን፡፡


የህጻናት ቀዶ ህክምና የሚደረግበት ጊዜ በራሱ ተጽእኖ አለው ፡፡ እንደበሸታው አይነት በተወለዱ 1 ሳምንት፤በ 6 ወርውሰጥ ወይም 1 ዓመት ተኩል ግዜ ውስጥ መታከም የሚኖርባቸው አሉ፡፡ ጊዜው ካለፈ ግን ኦፕሬሽኑ የማይሰራ ወይም የተወሳሰበ ሊሆን ይችላል፡፡ ያ ባይሆን እንኳን፣ ወይ እድገታቸው ይቀጭጫል ወይ በተደጋጋሚ ለኢንፌክሽን ይጋለጣሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙ ልጆች ህክምና ሳያገኙ ህይወታቸው ያልፋል ወይም እየተሰቃዩ ይኖራሉ፡፡ በልብ ህክምና ማዕከሉ ውስጥ እስከ 9000 የሚደርሱ ታካሚዎች ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ከነዚያ ውስጥ 6000 የሚያህሉት ህጻናት ናቸው፡፡ ወደፊት ደግሞ ፕሮግራሙ ሲሰፋ መሞት የሌለባቸውን ህጻናት በጊዜ ቀዶ ጥገና እየሠራን በCHD ምክንያት ህጻናት እንዳይሞቱ ማድረግ እንችላለን፡፡ ከመጀመሪያዋ ከተወለዱባት ቀን ጀምሮ ነው ስራው የሚጀምረው፡፡ ግን ለጊዜው ያንን አልፈው በህይወት የቆዩትን ልጆች መታደግ እንችላለን፡፡

ሀኪሞች:- የልብ ቀዶ ጥገና ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ ሀኪሞች እንዴት ስልጠና ሊያገኙ ይችላሉ?

ለምሳሌ እዚህ ሆስፒታል ሶስት የልብ ቀዶ ህክምና ሀኪሞች አለን፡፡ Intensivist, cardiac anesthesiologist የመሳሰሉት አሉን፡፡ እኛ ብዙ ሰው ማሰልጠን እንችላለን፡፡ አንድም፣ ሁለትም ሶስትም ሰው ብናሰለጥን ለሀገሪቱም ለሙያውም ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ወጣት የሆኑ ሀኪሞች ከዚህ በተጨማሪ መጥተው ልምድ መውሰድ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ ይሄን ሙያ ስማር፣ ሲሰራ አየቼ እንዲህ ነው ለካ ብዬ፣ እችለዋለሁ፣ ከኔ ጋር ይሄዳል ብዬ አይደለም፡፡ ለሌሎቹም እንደኔ መሆን አለባቸው ብዬ አላስብም፡፡ ሰዎች እዚህ መጥተው ሲያዩ የበለጠ ሊነሳሱ ይችላሉ ወይም ፐርሰናሊቲዬ ጋር አይሄድም ብለው እዚሁ ማቆም ይችላሉ፡፡ ይሄን በጊዜ ማወቅ ራሱ ጥሩ ጥቅም ይሰጣል፡፡

ውጪም ብዙ እድሎች አሉ፡፡ የተለያዩ ሀገራት፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ እስራኤል፣ አውስትራሊያ ካናዳ አሜሪካ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን መጀመሪያ እዚህ ሙያ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ጥሪያችንን ማወቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም በጣም ጊዜ የሚፈልግና ጫና ያለበት ስራ ነው፡፡ "ሀገርሽ ውስጥ ካሉት ጥቂት ባለሙያዎች አንዱ ሆነሽ ሌላ ቦታ ራስሽን ማግኘት የሆነ የሚያስገምት ነገር አለው፡፡
"

 ሀኪሞች:- የልብ ቀዶ ጥገና ትምህርት ለመማር የሚፈልጉ ሀኪሞች እንዴት ስልጠና ሊያገኙ ይችላሉ?

ለምሳሌ እዚህ ሆስፒታል ሶስት የልብ ቀዶ ህክምና ሀኪሞች አለን፡፡ Intensivist, cardiac anesthesiologist የመሳሰሉት አሉን፡፡ እኛ ብዙ ሰው ማሰልጠን እንችላለን፡፡ አንድም፣ ሁለትም ሶስትም ሰው ብናሰለጥን ለሀገሪቱም ለሙያውም ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንችላለን፡፡ ወጣት የሆኑ ሀኪሞች ከዚህ በተጨማሪ መጥተው ልምድ መውሰድ ይችላሉ፡፡ ለምሳሌ፣ እኔ ይሄን ሙያ ስማር፣ ሲሰራ አየቼ እንዲህ ነው ለካ ብዬ፣ እችለዋለሁ፣ ከኔ ጋር ይሄዳል ብዬ አይደለም፡፡ ለሌሎቹም እንደኔ መሆን አለባቸው ብዬ አላስብም፡፡ ሰዎች እዚህ መጥተው ሲያዩ የበለጠ ሊነሳሱ ይችላሉ ወይም ፐርሰናሊቲዬ ጋር አይሄድም ብለው እዚሁ ማቆም ይችላሉ፡፡ ይሄን በጊዜ ማወቅ ራሱ ጥሩ ጥቅም ይሰጣል

ውጪም ብዙ እድሎች አሉ፡፡ የተለያዩ ሀገራት፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ቻይና፣ እስራኤል፣ አውስትራሊያ ካናዳ አሜሪካ ሊሆን ይችላል፡፡ ግን መጀመሪያ እዚህ ሙያ ውስጥ ከመግባታችን በፊት ጥሪያችንን ማወቅ አለብን፡፡ ምክንያቱም በጣም ጊዜ የሚፈልግና ጫና ያለበት ስራ ነው፡፡፡፡

ሀኪሞች:- አጠቃላይ ለጤና ዘርፉ መሻሻል ምን አስተያየት ትሰጣለህ ?

የጤና ባለሙያዎች ስራችንን ወደንና አክብረን፤ የሰው ልጅ ህይወት ክቡር መሆኑን አውቀን መስራት አለብን፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የኛን አገልግሎት የሚፈልጉ ሰዎች ምስኪኖች (Desperate) ናቸው፡፡አብዛኛው የኢትዮጲያ ህዝብ የሚኖረው ገጠር ነው፤ እንደዚህ አይነት ሰዎችን መርዳት ሀላፊነታችን ነው፡፡ ይሄንም ሁሌም በልባችን ልንይዘው ይገባል፡፡ ይሄ እንዳይሆን የሚያደርጉ ብዙ ፈተናዎች አሉ በተለይም ወጣት ሀኪሞች ላይ፡፡ የክፍያ ሁኔታ ሊሆን ይችላል፣ የተሻለ ኑሮን መመስረት አለመቻል ሊሆን ይችላል፡፡ አንዳንዴ ራሴን እጠይቃለሁ ብዙ ሰዎች ለምን ወደውጪ ሀገር ለመሄድ ይፈልጋሉ እያልሁ፣ የተሸለ ህይወት ፍለጋ ነው፡፡ እኛ ባለሙያዎች ራሳችንን አስተካክለን፣ እንዲሁም ደግሞ እነዚህ ነገሮች ቢስተካከሉ በጤናው ዘርፍ ጥራት ላይ ትልቅ የሆነ አዎንታዊ ተጽዕኖ ይኖረዋል ብዬ አስባለሁ፡፡ ግን በሚያሳዝን ሁኔታ እኛ ቻ የምንወስነው ነገር አይደለም፡፡ ስለዚህ የመላውን የህክምና ማህበረሰብ እና የመንግስትንም ርብርብ ይጠይቃል፡፡

አሁን ብዙ ሀኪሞች ከሀገር ውጪ ያሉ ወደሀገር እየተመለሱ ነው፡፡ ውጪ ሀገር ያሉ ሀኪሞችም መምጣት ይፈልጋሉ መስራት ይፈልጋሉ፡፡ ብዙ ስራ ፈጣሪ ወጣት ሀኪሞች የተለያዩ ነገሮችን ለመስራት እየሞከሩ ነው፡፡ ሀኪም፤ ግዴታ ከታካሚ ጋር ቁጭ ብሎ መስራት የለበትም፤ በተለያየ መንግድ የጤና ዘርፉን ማሻሻል ይችላል፡፡ ግን ቅድም እንዳልሁሽ ሁሉም ሰው፣ ለወቀሳ ሳይሆን፣ በግላችን ከራሳችን ጀምሮ እስከ ሆስፒታላችን እንዲሁም ከጤና ጥበቃ ሚኒስትር እስከ መንግስት…ሁሉም ሰው የየራሱን ድርሻ ቢወጣ ብዙ ነገር ማስተካከል ይቻላል፡፡ 

ሀኪሞች:- ለወጣት ሀኪሞች ምን ትመክራለህ?

ይሄን ለማለት እድሜዬም ልምዴም ብዙ አይደለም፡፡ ግን እያንዳንዷን ከታካሚ ጋር የምናሳልፋትን ቀን አፕሪሸየት ማድረግ አለብን፡፡ አንድንድ ጊዜ ታካሚዎች ወይም አስታማሚዎች ካለማወቅ የሚናገሩት ነገር አለ ወይም አመለካከታቸው የተሳሳተ ሊሆን ይችላል፡፡ የኛ ሙያ ግን የተቀደሰ ሙያ ነው፡፡ ሰው ለመርዳት ትክክለኛውን በሽታና ህክምና ማወቅ አይጠበቅብሽም፡፡ትሁት መሆን፣ ከታካሚው ጋር ሆኖ ወርዶ ቁጭ ብሎ ማናገር፡ የበለጠ ጠቃሚ ነው ፡፡ በእርግጥ ብዙ የምንሰራቸው ነገሮች ይኖራሉ፤ ይደክመናልም ፡፡ ሆኖም ግን ቃላቶቻችን ዋጋ አላቸው፡፡

እንደተከበረ የማህበረሰቡ ክፍል ፤የሀኪም ቃላቶች ታካሚዎቻችንና ቤተሰቦቻቸውን ሊያጽናኑ ወይም ሊጎዱ ይችላሉ፡፡ ተጠንቅቀን መናገር አለብን፡፡ Empathy ያስፈልጋል፡፡ አይዞህ አይዞሽ መባባል የኢትዮጲያውያን ባህል ነው፡፡ ግን ደግሞ ከዚያም በላይ በህክምና ላይ ያስፈልጋል፡፡ ታካሚዎች አይገባቸውም ብለን ህመማቸውን በሚገባ አለመግለፅ አግባብ አይደለም፡፡ በተቻለ መጠን በሚችሉት ቋንቋና መንገድ፤ ምን እንደታመሙ፤ ምን የህክምና አማራጮች እንዳሉ እና የህክምና ውጤታቸውስ ምን እንደሆነ የመሳሰሉትን ነገሮችማሳወቅ ፤ አስፈላጊነቱን መረዳት አለብን፡፡ሀኪሞች:-ለወደፊት ምን ታስባለህ?

የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገናን የቀን ተቀን አገልግሎት እንዲሆን ማድረግ እፈልጋለሁ፡፡ ሁሉም ህክምናው የሚያስፈልገው ሰው ሊያገኘው ይገባል፡፡ ሁለተኛ ደግሞ ማስተማር እፈልጋለሁ፡፡ ብዙ የህጻናት የልብ ቀዶ ጥገና ትምህርቶች በ60ዎቹ ጭምር የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ውስጥ ተጀምረው አልተሳኩም፡፡ ለዚህ የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ የበጀት ማነስ፤የአቅርቦቶች አለመኖር፤ የባለሙያዎች ደስተኛ አለመሆን፣ የመሳሰሉት ችግሮች አሉ፡፡ እኔ እዚህ ስመጣ ለዚህ መሳካት አምስት አመት እመድባለሁ ብዬ ነው የመጣሁት፡፡ እና በእነዚህ አምስት አመታት ሁሉንም የሚያስፈልገውን ነገር ለማድረግ ዝግጁ ነኝ፡፡ ካልቻልሁ ያው ምን አደርጋለሁ… ግን በስራው ውስጥ የሚቀጥል ሌላ ሰው ማፍራት እፈልጋለሁ፡፡ ሁላችንም በዚህ ቦታ ያለን ሰዎች እንደኛ አይነት ሌሎች ሰዎች እንዲተኩ የማድረግ ሀላፊነት አለብን፡፡ ያኔ ብቻ ነው ያለምንም እፍረት አንገታችንን ቀና አድርገን መራመድ የምንችለው፡፡

ሀኪሞች:- በመጨረሻም የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ?

በልብ ቀዶ ጥገና ላይ ፍላጎት ያለው ሰው ካለ ወይም ማንኛውም የልብ ህመም ያለበት ታካሚ ያለው ሰው ካለ፣ አዋቂም ህጻናትም ቢሆኑ ወደልብ ማዕከላችን ሪፈር ማድረግ ይቻላል፡፡ በሙሉ ልባችን እንቀበላችኋለን፡፡ ኢትዮጲያ ውስጥ ብዙ ህክምና እየተሰጠ እንዳለ ሰው ማወቅ አለበት፡፡ለመማር የሚፈልግ ሰው ካለ ሙያችንን ለማስተላለፍ ስለምንፈልግ እና ግዴታችንም ስለሆነ ምክርና ስልጠና ለሚፈልግም ሰው፣ በልብ ማዕከሉ ታገኙናላችሁ፡፡

በመጨረሻም ይህ የሀኪሞች ፕላትፎርም የኢትዮጵያ ሀኪሞችን ለማቀራራብ እና ልምዳቸውን እንዲያጋሩ የመወያያ እድሎችን ስለሚያመቻች አድናቆቴን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡

ሀኪሞች:- በጣም እናመሰግናለን ዶክተር፡፡ 

Women Surgeons’ Experiences of Interprofessional W...
ከልብ ሕመም ለመታደግ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Friday, 01 July 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/