Featured articles

News

3 minutes reading time (521 words)

ዓይን ባንክ ለ2400 ዜጎች የብሌን ንቅለ ተከላ ተድርጎ ብርሃናቸው ተመለሰ አለ

images

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ዓለም አቀፍ እውቅና አጊንቷል።

የዓይን ባንኩ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር ቢሮ፣ ኮንኮርዲያ በተባለ መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና በቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ የሰዎችን ሕይወት ለማሻሻል በጥምረት ለሚሰሩ ስራዎች እውቅና በሚሰጡበት ፒስሪ ኢምፓክት አዋርድ (P3 IMPACT AWARD) እውቅና አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ከሰሃራ በታች ካሉ የአፍሪካ አገራት ውስጥ በብቸኝነት በአገር ውስጥ የዓይን ብሌን በመሰብሰብ ለንቅለተከላ ማዕከላት በማሰራጨት ለዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ድጋፍ እያደረገ የሚገኝ ተቋም ነው።

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ በዚህ ዘርፍ አሸናፊ መሆን የቻለው ከቀረቡት አምስት እጩዎች መካከል የተሻለ ተጽእኖ ፈጣሪ ሆኖ በመገኘቱ እንደሆነም ተገልጿል።

የዓይን ባንኩ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን በዓይን ብሌን ጠባሳ እና ተያያዥ ምክንያት የተከሰተውን ዓይነ-ስውርነት ለማጥፋት እያደረግ ባለው ጥረት እና አስተዋጽኦ ይህን እውቅና እንዳገኘ የድርጅቱ ደይሬክተር የሆኑት ለምለም አየለ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

 ''የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባደረጋቸው የቅንጅት ስራዎች ማለትም ከኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር፣ ዓይን ላይ የሚሰራ ሳይትላይፍ የተባለ የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት እና ሂማላያን ካታራክት ፕሮጀክት በአንድነት ባደረጉት ስምምነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን የዓይን ብሌን ጠባሳ አይነስውርነት ለመከላከል ባደረጉት የቅንጅት ስራ ነው ለ2020 የፒ3 ሽልማት የበቁት።''

የኢትዮጵያ የዓይን ባንክ ከ17 ዓመታት በፊት በአዲስ አበባ በዳግማዊ ምኒሊክ ሆስፒታል ግቢ ውስጥ አገልግሎቱን የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ግን ተጫማሪ አራት ቅርንጫፎችን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከፍቶ እየሰራ እንደሚገኝ ዳይሬክተሯ ነግረውናል።

''ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲተ ሆስፒታል፣ በትግራይ ክልል ቂሀ ሆስፒታል እና ሃዋሳ ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታል የዓይን ብሌን ንቅለ ተከላ ህክምና እንዲጀመር ተደርጓል''

ባለፉት 17 ዓመታት ውስጥም የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ለ2400 የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የብሌን ንቅለ ተከላ ተከናውኖላቸው ብርሃናቸው እንዲመለስ መደረጉንም ለምለም አየለ ነግረውናል።

በተጨማሪም በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከህልፈታቸው በኋላ የአይን ብሌናቸውን ለመለገስ ቃል እንደገቡ ገልጸዋል።

በዓለም ዙሪያ ከ12 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዓይን ብሌን ጠባሳ ምክንያት የሚሰቃዩ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ ወደ 300ሺህ የሚጠጉት ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የዓለም አቀፍ ትብብር ቢሮ፣ ኮንኮርዲያ የተባለው መንግሥታዊ ያልሆነ ድርጅት እና ቨርጂኒያ ዩኒቨርሲቲ በጋራ ባወጡት መግለጫ ላይ ጠቁመዋል።

ፒስሪ ኢምፓክት አዋርድ (P3 IMPACT AWARD) የሚባለው ሽልማት የሚሰጠው የህብረተሰቡን ችግሮች ለሚፈቱና እና ማህበረሰባዊ ግልጋሎት ለሚሰጡ የመንግሥት፣ የግል እና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችን ጥምረት ለማበረታታት ነው።

ዳይሬክተሯ እንደነገሩን የዓይን ብሌን ጠባሳና ተያያዥ ችግሮች የሰው ልጆችን ሙሉ ለሙሉ ማየት የተሳናቸው ያደርጋሉ። ''ነገር ግን ይህ ሙሉ በሙሉ ሊድን የሚችል ነው''

''ይህ ሊድን የሚችለው ደግሞ ሰዎች ከህልፈታቸው በኋላ በሚለግሱት የዓይን ብሌን አማካይነት ነው። ሰዎች ከሕልፈታቸው በኋላ የዓይን ብሌናቸውን ለኢትዮጵያ ዓይን ባንክ እንዲለግሱ ይጠይቃል፤ ባንኩ ደግሞ የሚለገሱ የዓይን ብሌኖችን ሰብስቦ፣ ንጽህናውና ጥራቱን ጠብቆ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ አረጋግጦ ህክምናውን ለሚያከናውኑ ተቋማት በማሰራጨት ሊድን በሚችል በሽታ አይነስውር ሆነው የተቀመጡ ዜጎችን ብርሀናቸው እንዲመለስ በማድረግ ላይ ነው የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ የሚሰራው'' ይላሉ ለምለም አየለ።

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ እንዲህ አይነት አለም አቀፍ እውቅናን ማግኘቱ ትልቅ ትርጉም እንዳለውም ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

''የህብረተሰቡ ግንዛቤ ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ባለበትና የሰውነት አካል ልገሳም ሆነ ንቅለ ተከላ ባህል ባልዳበረበት ሁኔታ ነው የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ እየሰራ የሚገኘው። ስለዚህ ይህን ሽልማት ማግኘታችን ትልቅ ኩራት ነው። ለወደፊት ለምንሰራው ስራም ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል ብለን እናስባለን።''

ደይሬክተሯ አክለውም እውቅናው በተለይ ደግሞ በአፍሪካ በዓይን ብሌን ልገሳና ንቅለ ተከላ ዘርፍ ፈር ቀዳጅ እንደመሆኑ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት ምሳሌ ለመሆንና የልቀት ማዕከል ለመሆን ለሚያደርገው ጥረት አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዓይን ባንክ ከ17 ዓመታት በፊት የተቋቋመ ተቋም ሲሆን ሲቋቋምም ዋና አላማው ሊድን በሚችል በብሌን ጠባሳና ተያያዥ ችግሮች የሚመጣ ማየት አለመቻልን ለመከላከልና ህክምናው በኢትዮጵያ እንዲጀመር ማድረግ ነበር።

መሠረታዊ ስራውም ሕብረተሰቡን ስለ ብሌን ልገሳ ማስተማር፣ ከትምህርት ባሻገር ደግሞ ከሕልፈት በኋላ የተለያዩ ፈቃደኛ ሰዎችን የዓይን ብሌን መሰብሰብ ከዚያም ንቅለ ተከላውን ለሚያከናውኑ የሕክምና ተቋማት ማሰራጨት ነው።

source

GUIDELINE WATCH 2020 by NEJM
Ethiopian Medical Women's Association(EMeWA) is ce...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Sunday, 16 January 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/