Featured articles

News

14 minutes reading time (2722 words)

"የጤና ስርአት ችግሮችን በጥልቀት የምናውቀው እኛው በመሆናችን፣ የመፍትሄ ሀሳቦችም ከኛ ነው የሚፈልቁት "

photo_2020-11-13_23-26-2_20201114-091235_1

 ሀኪሞች ዶት ኮም፣ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የአእምሮ ሀኪም እና ረዳት ፕሮፌሰር ከሆነችው ከዶ/ር አዜብ አሳምነው ጋር ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ ዶ/ር አዜብ በ2020 የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርን "EMA Young Physician Merit Award" አግኝታለች፡፡ በተጨማሪም የ "Mandela Washington Fellowship Alumni" ስትሆን በኢትዮጵያ ሴት ሀኪሞች ማህብር የ "Members admin and Public relations chair" ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ሎዛ አድማሱ እንደሚከተለው አዘጋጅታ አቅርባልናለች፣ ተከታተሉት፡፡

ሐኪሞች፡- ዶ/ር አዜብ ማን ነች? እራስሽን እንዴት ትገልጪዋለሽ?

ዶ/ር አዜብ፡- ከባድ ጥያቄ ነው፡፡ ሁልጊዜም ራሴን ነው የምገልጽበት መንገድ ይለዋወጣል፡፡ አሁን ራሴን የማየው፣ ሁልጊዜ መማር ሁልጊዜ መለወጥ እንደምትፈልግ ሰው ነው፡፡ ግን ራሴን የምገልጽበት ነገር አንድ ብቻ እንዲሆን አልፈልግም፡፡ ስለራሴ ሳስብ የምጠይቃቸው ሀሳቦች "የማውቀውን ነገር ምን ያህል አካፍያለሁ? ምን ያህልስ አገልግያለሁ?... በዚህ አጭር ህይወት፣ ምን ያህል በጎ ተጽእኖ ፈጥሬያለሁ? ከኔ የሚጠበቀውን ነገር አድርጌያለሁ ወይ?" የሚሉትን ነው፡፡

ሐኪሞች፡- ይህ ከሙያሽ ጋር በተለይም ሳይካትሪስነትሽ [የአዕምሮ ህክምና ስፔሻሊስትነት] የተገናኘ ነው ማለት እንችላለን ?

ዶ/ር አዜብ፡- ይመስለኛል፡፡ ሀኪምነት በራሱ እንደዚያ ነው፡፡ ሌሎችን ማገልገልን፣ ውሳኔ መስጠትን ይጠይቃል፡፡ በፊት ዘጠነኛ ክፍል ተማሪ እያለሁ፣ ሳይኮሎጂስት [የስነልቦና ባለሙያ] መሆን እፈልግ ነበር ፡፡ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ሁልጊዜ ቤታችን ውስጥ ይመጣ ነበር እና የእሁድ እትማቸው ላይ ስነልቦናን የተመለከተ አንዲት ገጽ ነበራችው፤ 'ህይወት እንዲህ ናት' የሚል፡፡ በጀርባ ደግሞ ስነጽሁፍ አለ፡፡ ግጥም እና የመሳሰሉት የሚወጣበት፡፡ እዚያ ላይ ግጥምም ልኬ አውቃለሁ፡፡ ምንም እንኳን ልጅ ብሆንም፣ እዚህኛው ገጽ ላይ የማነባቸው ነገሮች ግን እንዳስብ፣ እንዳሰላስል ያደረጉኝ ነበር፡፡ ለምሳሌ ትዝ የሚለኝ "ንዴት ራሳችን ነን የምንፈጥረው" የሚል ሀሳብ ያለው ጽሁፍ ነበረ፡፡ እናም ይሄ ለእኔ አዲስ ሀሳብ ነበር፡፡ እንዴት ነው ራሳችን ላይ ንዴት የምንጨምረው ሚለው ነገር ወደራሴ እንድመለከት አድርጎኝ ነበር፡፡ እነዚህን በማንበቤ ራሴን አሳድጌበታለሁ፡፡ሌሎች ሰዎች ግን እንዲህ አይነት እድል ላያጋጥማቸው ይችላል፤ ማንበብ ላይችሉ ይችላሉ፤ ጋዜጣውን ላያገኙ ይችላሉ፤ ምንም የሚያውቁት ነገር ላይኖር ይችላል፡፡ እኔም እዛ ላይ ስላነበብሁት ነው ያንን ያወቅሁት፡፡ በዚህ ረገድ ሰዎችን እኔም መርዳት እነዳለብኝ አስብ ነበር፡፡ ጽሁፎቹ ፤ "ሳይኮሎጂስቶች፣ ፈላስፋዎች፣ ሳይካትሪስቶች …" በማለት ይጠቀሱ ስለነበር፣ ማንነታቸውን የማውቅ ጉጉት አደረብኝ እናም አባቴን ጠየቅሁት፡፡ እሱም "ፈላስፋዎች እና ሳይኮሎጂስቶች ዩኒቨርሲቲ ላይ አስተማሪ መሆናቸውን ነው የማውቀው፤ ሌሎቹ ዶክተሮች ሳይሆኑ አይቀሩም" አለኝ፡፡ ከዚያ የሶስቱን ልዩነት ከመስሪያ ቤት በኢንተርኔት ፈልጎ ፕሪንት አድርጎ አመጣልኝ፡፡ ከዚያም ከሶስቱ አወዳድሬ ሳይካትሪስት ሳይሻል አይቀርም ብዬ አስብኩ፡፡

ሳይካትሪ ውስጥ ከባድ የአእምሮ ህመም ያለባቸውን ሰዎች የማግኘት እድሉ ይኖርሀል፡፡ ወደአንተ የሚመጡት በጣም የተጎዱት፣ በጣም የታመሙት፣ ሰው የማይደርስላቸው ናቸው፡፡ ሌላው ታካሚ ብዙ ጊዜ ሲጮህ ወይ ሲያለቅስ ይሰማል፣ ትኩረት ያገኛል፤ እነዚህ ሰዎች ግን ብዙ ጊዜ የማይደመጡ እና ቢጮሁም ማንም የማያስተውላቸው አይነት ናቸው፡፡ በዚህ ሙያ ባልሰማራ እንኳን ተገቢው ትኩረት ያላገኘ ወደሚመስለኝ የስራ አይነት የምሳብ ይመስለኛል፡፡ ሳይካትሪ ራሱም እንደዛ ነው፡፡ ለምሳሌ ደብረማርቆስ ከመሄዴ በፊት የት አካባቢ ነው ሳይካትሪስት ሆኜ ብሰራ በደንብ ተጽዕኖ ማምጣት የምችለው ብዬ አጣርቼ ነበር የሄድኩት፡፡

"የጤና ስርአቱን ለማሻሻል፣ መንግስት የባለሙያዎችን ጥያቄ ማዳመጥ እና መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ደግሞ እኛም እንደሀኪም ባለቤትነት ሊሰማን ይገባል፡፡ ችግሩን በጥልቀት የምናቀው እኛው በመሆናችን፣ የመፍትሄ ሀሳቦችም ከኛ ነው የሚፈልቁት ብዬ አስባለሁ፡፡ በተደራጀ እና ግልጽ በሆነ መልኩ፤የመንግስት ሀላፊዎች ተቀበሉንም አልተቀበሉን፤የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ አለብን፡፡ "

ሐኪሞች፡- ስለዚህ ላንቺ ተጽዕኖ ማምጣት ከገንዘብ በላይ ዋጋ አለው ማለት ነው?

ዶ/ር አዜብ፡- አዎን እኔ እንደዛ ነው የማስበው፡፡ በእርግጥ ገንዘብ ሲኖርህ፤ ለውጥ ለማምጣት የበለጠ ሞራል ይኖርሀል፡፡ ገንዘብ ራሱ የራሱ የሆነ ተጽዕኖ አለው፣ ግን አእምሮዬ በዚያ በኩል አያስብም፡፡ የተሻለ ለውጥ ማምጣት የምችልበት ቢሆን ወይም ደግሞ ትኩረት የተነፈጋቸው፣ የተገፉ ማህበረሰቦችን ማገልገል ወይም እንደዛ ዐይነት ስራ ላይ መስራት እመርጣለሁ፡፡

ሐኪሞች፡- እስቲ ስለትምህርትሽ አጫውቺን?

ዶ/ር አዜብ፡- ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በፈረንጆች 2013 ዓ.ም. የህክምና ትምህርቴን ጨርሼ፣ ከዚያ ለስራ ተመድቤ የሄድሁትደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ ነው፡፡ ወደዚያ የሄድኩበት ምክንያት ወዲያውኑ የሳይካትሪ ስፔሻሊቲ የሚያስተምረኝ ቦታ የት ነው ብዬ ሳጠያይቅ፣ ደብረማርቆስ ዩኒቨርስቲ የማስተማር ፍላጎት እንደነበረው ስለተረዳሁ ነበር፡፡ በዚያ ጊዜ የሬዚደንሲ [ስፔሻላይዜሽን] ትምህርት ለመጠየቅ ቢያንስ አንድ አመት ወይ ሁለት አመት መስራት ግዴታ ነበር፡፡ ስለዚህ በፍጥነት የትምህርት እድሉን ለማግኘት ማሳመን ነበረብኝ፡፡ በወቅቱ በክልሉ ምንም ሳይካትሪስትአልነበረምና ለመጠየቅ ምክንያት ነበረኝ፡፡ የፋርማኮሎጂ ሌክቸረር ስላልነበረ፣ ለትምህርት እስከምሄድ ድረስ ለስድስት ወር አስተምሬ ነበር፡፡ ጠቅላላ ሀኪም ሆነህ ፕሪክሊኒካል ስታስተምር፣ እያነበብክና አብረህ እየተማርክ ነው፤ ሆኖም ክሊኒካል አተያይ ያለህ በመሆኑ ለተማሪዎች የሚጠቅም ነገር አለው፡፡ ከዚያ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሳይካትሪ ዲፓርትመንት የመግቢያ ፈተና አልፌ ሬዚደንሲ ጀመርኩኝ፡፡

ሐኪሞች፡- ሳይካትሪ ስትጨርሺ ተመልሰሽ ሄድሽ ማለት ነው?

ዶክተር አዜብ፡- አዎ፡፡ ተመልሼ ሄድሁኝ፡፡ ለብዙ ሰው ተመልሶ መሄድ የሚፈለግ ነገር አይደለም፤ እኔ ግን ተመለስሁ፡፡ ምክንያቱም የገባሁትን ቃል መጠበቅ ነበረብኝ፡፡ ሁለተኛ ደግሞ አዲስ ቦታ ደግሞ አዲስ ነገር መስራት ጥሩ ልምድ ነው በሚል እስከ ህዳር 2012 መጨረሻ ድረስ እዚያ ቆየሁ፡፡ አሁን ጥቁር አንበሳ ነው ያለሁት፡፡ 


"
ሀኪም በማህበረሰቡ የሚታይበት ቦታው ትልቅ ስለሆነ፡ "ሌሎች ከባባድ ጉዳዮች እያሉ እንዴት ስለዚህ ነገር/ትንኮሳ/ ስሞታ ይቀርባል?" ይባላል፡፡ ግን አንዲት ሴት ከታች ለሚመጡ ሴቶች አርአያ መሆን ካለባት ሁሉም ነገሮች ሊስተካከሉላት ይገባል፡፡ ሴቶች ወደመሪነት ደረጃ ይምጡ ሲባል፣ ምንድን ነው እንዳትመጣ ያደረጓት ነገሮች የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡"

ሐኪሞች፡- በሀገራችን ውስጥ የሳይካትሪ ሞያ እና ስልጠና ምን ደረጃ ላይ ያለ ይመስልሻል?

ዶክተር አዜብ፡- ስለእኛ ሀገር ለመናገር ትኩረት ካልተሰጣቸው ሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ትንሽ ባለሙያ ነው ያለው፡፡ የአእምሮ ህክምና ስፔሻሊስት የሆንን ከ90 በታች ነን፡፡አብዛኛው፣ ወደ 60 የሚሆነው ደግሞ አዲስአበባ ነው ያለው፡፡ ምናልባት አብዛኛውን አሁን ያለውን የአእምሮ ጤና ህክምና የሚሸፍኑት ከሳይካትሪስት ውጪ የሆኑ የሳይካትሪ ባለሙያዎች፣ ማለትም በማስተርስም፣ በመጀመሪያ ዲግሪም በዲፕሎማ ደረጃ የተማሩ ናቸው፡፡ ህክምናው በደንብ እንዲሰጥ ክሊኒካል ሳይኮሎጂስት [የስነልቦና ህክምና ባለሙያ]፣ የሶሻል ወርክ [የማህበራዊ አገልግሎት] ባለሙያም ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ደግሞ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው እነሱም በአዲስ አበባ ነው ተከማችተው ያሉት፡፡ ከባለሙያዎች እጥረት በተጨማሪ የትምህርት ቤቶች እጥረት አለ፡፡

በማህበረሰባችን ደረጃ ደግሞ የአእምሮ ጤና ግንዛቤም አልተስፋፋም፡፡ ሌላውም ህክምናው ራሱ ቀስ በቀስ ነው ወደዚህ ደረጃ የደረሰው፣ ከባህላዊ ህክምና ወደ ዘመናዊ ህክምና ወይም ሁለቱንም እየተጠቀመ፤ ሙሉ በሙሉ ወደ ዘመናዊው ህክምና ለመቀየር በጣም ብዙ ጊዜ ፈጅቶበታል፡፡ ለእእምሮ ህክምናም አብዛኛው ሰው ጸበል ቦታ ወይም ባህላዊ ሀኪሞች/ አዋቂ የሚባሉ ሰዎች/ ጋር ሄዶ ገንዘቡን እና ጉልበቱን ጨርሶ፣ ህመሙ በጣም ተባብሶ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ከደረሰ በኋላ ነው ወደእኛ ህክምና የሚመጣው፡፡ እነኚህ ሁሉ ሙያው ላይ ያሉ ተግዳሮቶች ናቸው፡፡

በዚያው ልክ ደግሞ በአእምሮ ጤና ጥናት በጣም የታወቁ ትልቅ ቦታ ያሉ ባለሙያዎችም በሀገራችን ውስጥ አሉ፡፡ ለምሳሌ የኔ መምህራንም የነበሩት ፕሮፌሰር አታላይ አለም በሰሯቸው ጥናቶች፣ በጣም ትልቅና የሚከበሩ፣ በአፍሪካም በአለምም የታወቁባለሙያ ናቸው፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ከሳይካትሪስትነት በተጨማሪ የሐገር ሽማግሌ ናቸው፡፡ የአእምሮ ጤና ላይ በጣም ብዙ ስራ ሰርተዋል፡፡ እነኚህ ሁለቱ በተለይ የአማኑኤል ሆስፒታልን በመቀየር፣ ትምህርት እንዲጀመር በማድረግ በጣም ትልቅ ሚና የተጫወቱ ሰዎች ናቸው፡፡ ሬዝደንት ሆኜም ጥናት ስሰራ ያገዙኝ እነኚህ ሁለቱ ናቸው፡፡ ዶክተር አበባው ፍቃዱ እና ባለቤቱ ዶ/ር ሻርሎት በአእምሮ ጤና ምርምር ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡ እንዲሁም ዶክተር ሰለሞን ተፈራ በጣም ትልቅ የጥናት ፕሮጀክት አለው፡፡ ስለዚህ በጣም ደስ የሚሉ ነገሮች አሉ፣ በተለይ በጥናትና በምርምር በኩል በጣም ትልልቅ ክሊኒካል ትራያሎችንም ይሰራሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች በጣም አበረታች ናቸው፡፡ በአገልግሎት በኩል ግን ብዙ ይቀረናል፡፡ 

 ሐኪሞች፡- በህሙማን ግልጋሎት በኩል ምን ይጎድለዋል? መድኃኒቶች ላይ ወይም ፕሮሲጀር ላይ?

ዶክተር አዜብ፡- ለምሳሌ እኔ የሬዝደንሲ ጥናቴን እ.ኤ.አ 2016 ላይ በElectroconvulsive therapy (ECT) [የንዝረት ህክምና] ላይ ነበር የሰራሁት፡፡ የአምስት አመታት መረጃ ወስጄ ነበር ያጠናሁት፡፡ "የECT አገልግሎት ምን ያህል ይሰጣል?"፤ "ለምን አይነት ህመሞች ይሰጣል?" የመሳሰሉትን ነገሮች፡፡ ይህ አገልግሎት አንድ ቦታ ላይ ማለትም በአማኑኤል ሆስፒታል ብቻ ነበር የሚገኘው፡፡ ከዛ በኋላ ኤካ ኮተቤም ይሰጥ ነበር፡፡ ስለዚህ ቢበዛ ሁለት ቦታ ነው ያለው፡፡ ለሀገሪቱ በሙሉ ማለት ነው፡፡ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከECT ውጪ EEGም በጣም አስፈላጊ ነው፡፡ እንደ CT እና MRI ያሉት ሁልጊዜም ቢኖሩ ጥሩ ነው፡፡ ከዚያ ውጪ የመድኃኒት አማራጮችም በጣም ትንሽ ናቸው፡፡ እኔ ሬዚደንት ከነበርኩበት አንጻር፣ አሁን የተሻለ ቢሆንም፣ አለም ካለበት ደረጃ አንጻር በጣም ብዙ የሚቀረን ነገር አለ፡፡

ሌላው ደግሞ የአእምሮ ህክምና የሚሰጥበት ቦታ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች አብረው ሊኖሩ ይገባል፡፡ ምክንያቱም የአእምሮ ህመም ምልክቶች የሌሎች ህመሞች ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ወይም የሌሎች ህመሞች ምልክት የአእምሮ ህመም ማሳያ ሊሆን ይችላል፡፡ አንድ ላይም ሊፈጠሩ ይችላሉ፡፡ አንዱ ሌላኛውን ሊያባብስ ይችላሉ፡፡ ከዚያም በተጨማሪ መገለል አለ፡፡ ለምሳሌ አንድ ሰው አማኑኤል ገባ ከተባለ በቃ ክፉ ቦታ ገባ እንደማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ በማንም አይታይም አይሰማም ተብሎ ይገመታል፡፡ እንደዚህ ያሉ ነገሮችን ለመቀነስ እና የአገልግሎቱን ተደራሽነት ለመጨመር ከሌሎች የህክምና አገልግሎቶች ጋር አንድ ላይ ቢሆን ጥሩ ነው፡፡

ሐኪሞች፡- ሌሎች የህክምና አማራጮችስ እንዴት ናቸው? እንደ የንግግር ህክምና (psychotherapy) ያሉት?

ዶክተር አዜብ፡- ከሌሎች ባለሙያዎች ጋር በትብብር መስራት ያስፈልጋል። ብዙ ሳይካትሪስት በፋርማኮቴራፒ [በመድሀኒት ህክምና]ም በሳይኮቴራፒ [በንግግር ህክምናም] ይሰለጥናል፡፡ ቁጥራችን ግን ውስን ስለሆነ ሁሉን ነገር ሁልጊዜ ለብዙ ሰው መስራት አስቸጋሪ ይሆናል ፡፡ ስለዚህም በሳይኮቴራፒ ብቻ የሰለጠኑ ሰዎች ቢኖሩ በደንብ መተጋገዝን ይፈጥራል፡፡ ሶሻል ወርከር ደግሞ በብዛት ቢኖሩ፣ በተለይም በህክምና ዙርያ የሰለጠኑት ቢኖሩ እኛ አክመን ያመጣናቸውን ሰዎች ቤታቸው ሄደው በመከታተል 'እንዴት ናችሁ' በማለት፣ የሚያስፈልጋቸውን ማህበራዊ ነገሮች ማሟላት ይችላሉ፡፡ምክንያቱም የአእምሮ ህመም የሚታከመው ባዮሳይኮሶሻል ሞዴልን በመከተል ነው፡፡ ይህ ማለት አንድ የአእምሮ ህመም እንዲከሰት ተፈጥሯዊ መንስኤ (biological factor)፤ የስነልቦና መንስኤ (psychological factor)፤ ማህበረሰባዊ መንስኤ (social factor) አለው፡፡ ማህበራዊ መንስኤ ውስጥ ባህል፣ መንፈሳዊነት እና የመሳሰሉት ይካተቱበታል፡፡ ስለዚህ እነኚህን ሁሉ ያላከተተ እገዛ በቂ አይሆንም እና ሁሉም ነገር በሳይካትሪስት መሰጠት ይችላል ብዬ አላምንም፡፡ የባለሙያች ትብብር በጣም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ በተቋማት ደረጃም ትብብር ያስፈልጋል፡፡ ከፖሊስ ጋር፣ ከወረዳ እና ከቀበሌ ጋር መቀናጀት ያስፈልጋል፡፡ በደንብ ከተሰራ ዘላቂ የሆነ ውጤት ይኖረዋል፡፡

" ሌላ ታካሚ ብዙ ጊዜ ሲጮህ ወይ ሲያለቅስ ይሰማል፣ ትኩረት ያገኛል፤ እነዚህ የአእምሮ ህመም ታካሚዎች ግን ብዙ ጊዜ የማይደመጡ እና ቢጮሁም ማንም የማያስተውላቸው አይነት ናቸው፡፡

የአእምሮ ህክምና የሚሰጥበት ቦታ ሌሎች የህክምና አገልግሎቶች አብረው ሊኖሩ ይገባል፡፡ "

 ሐኪሞች፡- እስቲ ስለ "YALI –Young African Leadership Initiative "ንገሪን፡፡ አንድ ሀኪም እዚህ ውስጥ በመሳተፍ ምን ይጠቀማል?

ዶ/ር አዜብ፡- ከትምህርት ውጪ ባሉ እንቅስቃሴዎች ላይ መሳተፍ የጀመርሁት ከህክምና ትምህርት ቤት ጀምሮ ነው፡፡ የሕክምና ትምህርት ቤት የሚጨንቅ አይነት አካባቢ ነው፤ ለኔ ይሄ በጣም ምቹ አልነበረም፡፡ የእኔ ስብዕና ማበረታቻ ይፈልጋል፤ ሕክምና ትምህርት ላይ ደግሞ ወቀሳ ይበዛዋል፡፡ በእርግጥ በዚህ አቅጣጫም አንዳንድ ጥሩ የምላቸው ሲኒየሮች ነበሩ፡፡ ብቻ ይህንን አሉታዊ የሆነ ነገር የምቋቋምበት መንገድ እፈልግ ነበር፡፡ ለራሴ ጥሩ ስሜት እንዲሰማኝ እና አቅም እንዲኖረኝ እፈልጋለሁ፡፡ስለዚህ የኢትዮጲያ ህክምና ተማሪዎች ማህበር ላይ መሳተፍ ጀመርሁ፡፡ እና እየተሳተፍሁ የተረዳሁት ሐኪም ለመሆን ከ ክሊኒሻንነት [ህክምና ከመስጠት] አና ከሪሰርቸርነት [ጥናቶችን ከማካሄድ] ባሻገር የሚያስፈልጉ፣ ትምህርት ቤት ውስጥ የማንማራቸው ክህሎቶች አሉ፡፡ስለዚህ ስለሊደርሺፕ [አመራር]የመጀመሪያ ሀሳብ ያገኘሁት ከዚያ በወሰዱኩት ስልጠና ነበር፡፡ የተግባቦት፣ የድርድር እና በጋራ የመስራት ክህሎቶች እንደሚያስፈልጉ ተረዳሁ፡፡ ምክንያቱም ሐኪም አንድ ቡድንን ይመራል ተብሎ ነው የሚጠበቀው፡፡ ስለዚህ የመምራት ችሎታ ከሌለህ፣ የመነጋገር ልምዱ ከሌለህ፣ ቅራኔን መፍታት ካልቻልህ ስራው አይሰራም ማለት ነው፡፡ እና በነዚህ ልምዶች ምክንያት እነኚህን ነገሮች እያስተዋልሁ መጣሁ፡፡ ሌሎችም የወሰድኋቸው ስልጠናዎችም ነበሩ፡፡ "Active citizens" የሚባል የBritish Council ስልጠና ስለፕሮጀክት አመራር ወስጄ ነበር፡፡ ስለዚህ አስፈላጊነቱን ቀድሜም ተረድቼው ነበር፡፡

እናም ስለYoung African Leadership Initiative (YALI) Mandela Washington Fellowship Program የሰማሁት በአጋጣሚ ሰለ የአእምሮ ህክምናን ማሻሻል በተመለከተ አዕምሮ ጤና ፒኤች ዲ ከምትማር ሶሻል ወርከር ልጅ ጋር ስናወራ ነበር፡፡

ብዙ ጊዜ መምራት "leardership" ሲባል የምናስበው ስለ ስልጣን ነው ግን ከዛ የተለየ ነው፡፡ እኔ የተወዳደርኩት በፈረንጆች 2018 Public Management Institute ላይ ነው፡፡ ያም ማለት ባለህበት ስራ ላይ፣ የመንግስት ስራ ቦታ ላይም ቢሆን፣ ብቻ "ባለህበት ቦታ ለውጥ ለማምጣት ትሞክራለህ ወይ?" ብሎ ነው የሚጠይቅህ፤ ያንን ካደረግህ መሪ ነህ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በፊት የጀመርካቸውን ጥረቶች እንድታሳይ ያስፈልጋል፡፡ የፕሮግራሙ አላማም ጥረትህን መደገፍ ነው፡፡ በእርግጥ ሌሎችም ቢዝነስ፣ በጎ ፈቃደኛ ስራዎች የመሳሰሉት መስኮች/Tracks/ አሉት፡፡"በሂደት የተረዳሁት ትልቁ ነገር ግን በጣም ጥሩ ግንኙነት መረብ /Networking/ ክህሎት ባህል የለንም፡፡ ስለምንሰራው ስራ አንተዋወቅም፡፡ "

እኔ የቆየሁበት ሀዋርድ ዩኒቨርስቲ፣ ዋሽንግተን ዲሲ ነው የሚገኘው፡፡ ከ19 የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከመጡ ሰዎች ጋር ነው ያሳለፍነው እና በጣም ደስ የሚል ልምድ ነበር፡፡ "እንዴት ነው ፐብሊክ ኢንቲትዩት የሚመራው?" ከሚለው አንጻር፤ የእነሱን ልምድ ሰማን፡፡ አንዳንድ ጠቃሚ መንገዶችን አሳዩን፡፡ በዚህ ሂደት ውስጥ ትልቁ የተረዳሁት ነገር ግን እነሱ በጣም ጥሩ ግንኙነት መረብ /networking/ ክህሎት እነዳላቸው ነው፡፡ እኛ ይህ ባህል የለንም፡፡ እኛ እዚሁ ሀገር ውስጥ ሆነን ፣ ስለምንሰራው ስራ አንተዋወቅም፡፡ የሆነ ሰው ፣ ሌላ ቦታ ሄዶ እውቅና ሲሰጠው ነው፣ ትዝ የሚለንና "ለካ ይህ ሰው ትልቅ ነው?" የምንለው፤ ወይም ፈረንጅ ሲያከብረው፡፡ ግን እዚህ ብንተዋወቅ እርስበእርስ መደጋገፍ እና ብዙ መስራት የምንችለው ነገር ይኖራል፡፡ ከፌሎውሺፑ ስንመለስ በዚያ ባች ከተሳተፉት 40 ሰዎች ውስጥ በተለያዩ መስኮች የቆየን 10 ሀኪሞች ነበርን፡፡ በተለያየ ዩኒቨርስቲ፣ የተለያየ ስራ የምንሰራ ቢሆንም የኛን ችሎታ አንድ ላይ ብንሰበስበው ከዚያ ያገኘነውን ትምህርት በመጠቀም የተሻለ ነገር ለመስራትና ለውጥ ለማምጣት እድል ይሰጠናል ብለን፣ በ አሜሪካ ኤንባሲ ስምምነት፣ ማንዴላ ኢትዮጲያ ዶክተርስ ብለን ስብስቡን መሰረትን፡፡

ሀኪም መሆን መሪነት ነው፡፡ ምንድን ነው የኔ ጠንካራ ጎን፣ የትኛውን ባዳብረው ጥሩ ነው፣ የትኛው ይጎድለኛል፣ የሚሉትን ካወቅን ለፌሎውሺፑ ለመወዳደር ቀላል ነው፡፡ ከኛ በኋላም ከኛ በፊትም ብዙ ሀኪሞችም ሄደዋል፡፡ ከ35 አመት በታች የሆኑ ሰዎች መወዳደር ይችላሉ፡፡ ሀኪም ሆነህ የተሻለ ሀኪም መሆን፣ በክሊኒካል ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዘርፍ የተሻለ ለመሆን የሚቻልበት ጥሩ አጋጣሚ ነው፡፡ ሁሉን አቀፍ የሆነ ሀኪም ለመሆን፣ ልክ WHO "5 ስታር ሀኪም" እንደሚለው ለመሆን ያስቸላል ብዬ አስባለሁ፡፡

በተጨማሪም የYALI የምስራቅ አፍሪካ ማዕከል በናይሮቢም ሰላለው እዚያም ስልጠናዎች በመውሰድ በ አስተዳደራዊ ሲስተማችን ያለትን ችግሮች ለመፍታት ጥረት ማድረግ ይቻላል፡፡ ስለዚህ "የኔ ድርሻ ምንድን ነው? እኔ ምን ማድረግ እችላለሁ?" የሚል ጥያቄ በውስጣቸው ያላቸው ሰዎች በሙሉ ቢሳተፉበት ይጠቀማሉ ብዬ ነው የማስበው፡፡


Book recommended by Hakimoch. Download the PDF by clicking the image.


"መምራት "Leardership" ሲባል የምናስበው ስለ ስልጣን ነው ግን ከዛ የተለየ ነው፡፡...."ባለህበት ቦታ ለውጥ ለማምጣት ትሞክራለህ ወይ?" ...ያንን ካደረግህ መሪ ነህ ማለት ነው፡፡ "  


ሀኪሞች፡- "Hear me too"["እኔንም ስሙኝ"] ዘመቻ በማንዴላ ኢትዮጲያ ዶክተርስ ምን ምን ሰራችሁ?

ዶ/ር አዜብ፡- UN women ባልሳሳት November ላይ የ16 days of activism የሚል ዘመቻ አላቸው፡፡ በዚያ ጊዜ ላይ ማንም ሰው ዘመቻውን መቀላቀል ይችላል፡፡ እኛ ዘመቻውን ስንጀምር፣ እነርሱ በወቅቱየነበራቸው ርዕስ ጾታዊ ጥቃት ነበር፡፡ የማንዴላ ኢትዮጲያ ዶክተርስም ምን ማድረግ እንችላለን ብለን አሰብን፡፡ ከዛ በፊትም ብዙ የሰማናቸው በሀኪሞች ላይ የሚደርሱ የጾታዊ ጥቃት ታሪኮች ስላሉ ለምን ተጨማሪ ታሪኮች አንሰበስብም ብለን በኔትወርኮቻችን አፈላለግን፤ እናም በጣም ብዙ ታሪኮች ተላኩልን፡፡ ሰዎች ታሪካቸውን ለማውጣት በጣም ይፈራሉ፤ ስለዚህ ማንነታቸው ሳይታወቅ በኛ ገጽ እና ከሀኪም ገጽ ጋር በመተባበር ታሪኮቹ እንዲወጡ አደረግን፤ ጥሩ ምላሾችም አገኘን፡፡ አንደኛ ሰዎች ስለጉዳዩ እንዲያውቁ አደረግን፡፡ በዚህም ምክንያት አንዳንድ የትምህርት ቤት አስተዳዳሪዎች ምላሽ ሰጡ፡፡ እንዲህ ያለ ነገር እንዳለ አናውቅም ነበር፤ እንወያይበት አሉ። አንዳንዶች ደግሞ ማድረግ የሚችሏቸውን ነገሮች አግዘውናል፡፡ ለምሳሌ፡ በጊዜው የጴጥሮስ ሆስፒታል አስተዳዳሪ የነበረው አቶ ያዕቆብ ሰማን እንዲሁም በአዲስአበባ ዩኒቨርሲቲ የአጥንት ህክምና ስፔሻሊስት ዶክተር ብሩክ ላምቢሶም በወቅቱ አግዘውናል፡፡ከዚያ በኋላ አሁን በጥቁር አንበሳ በሬዚደንሲ ስልጠና ውስጥ ስልጣንዎች እና ውይይቶች ተጀምረዋል:: መቀሌ የሴቶች ግሩፕ የሚባልም አለ፤ አይደር ሆስፒታል ያሉ የህክምና ተማሪዎች እና ሀኪሞች የመሰረቱት ቡድን ነው፡፡ ችግሮችን ለመፍታት ይሞክራሉ፣ ይወያያሉ፡፡ የሆነ የፈጠርነው ተጽእኖ አለ ብዬ አስባለሁ፡፡ እኛ ደግሞ በራሳችን የፓናልውይይቶች አካሂደን በተቀመጡት የመፍትሔ ሀሳቦች መሰረት በየተቋማት ስለጾታዊ ጥቃት መመሪያ ያስፈልጋል በሚል ተስማምተናል፡፡ አሁን ብሮሸሮችን አዘጋጅተናል፣ ማሰራጨት ነው የቀረን፡፡

ሀኪሞች፡ በህክምና ውስጥ ስላሉ የጾታዊ ጥቃቶች ወይም ትንኮሳዎች አብራሪልን

ዶ/ር አዜብ፡- የጾታ ጥቃት ወይም ትንኮሳዎች /Harrassment/ ስንል የሚገልጹት ነገር ይለያያል፡፡ ትንኮሳዎች ስንል ጥቃቅን ነገሮች ውስጥ ጭምር ውስጥ እንገባለን፡፡ መደፈር እና መጠለፍ ትላልቅ ነገሮች ናቸው፡፡ ትንኮሳ በጾታህ ምክንያት ብቻ ስራህን በአግባቡ እንዳትሰራ ቀን ተቀን የሚያጋጥምህ ችግር ጭምር ነው፡፡ ለምሳሌ በሆስፒታል ብንጀምር ኢንተርን እና ሬዝደንት ግንኙነትን ብንመለከት፤ ለማማከር ሲባል ስልክ ይሰጣል፤ ያ ስልክ ግን አላግባብ ይጠቀሙበታል፡፡ ስልክ የምትለዋወጠው በታካሚው ላይ ለመወያያት ነው ግን እየቆየ ጓደኛ እንሁን፣ እንገናኝ፣ የሚል ጭቅጭቅ /ትንኮሳዎች/ይከሰታል፡፡ ይህ ምንድን ነው የሚያሳድረው ተጽእኖ? የአስተማሪ እና የተማሪ ግንኙነት ስላለ እሱን ካላደረግሁ ውጤቴ ሊበላሽ ይችላል የሚል ሀሳብ ይፈጥርና በነገሩ ለመስማማት መገደድን ይፈጥራል፡፡ ስራ ላይ የማተኮር ነገርንም ይቀንሰዋል፡፡ይሄ ስጋት ብቻ አይደለም፣ ይፈጠራልም፡፡ አልፈልግም ስላሉ ብቻ ውጤታቸው ሲበላሽ ያየናቸው ሰዎች አሉ፡፡ ግን እነኚህን ነገሮች በግልጽ ለማውራት ይከብዳል፡፡ ምክንያቱም ሀኪም በማህበረሰቡ የሚታይበት ቦታው ትልቅ ስለሆነ፡፡ "ሌሎች ከባባድ ጉዳዮች እያሉ እንዴት ስለዚህ ነገር/ትንኮሳ/ ስሞታ ይቀርባል?" ይባላል፡፡ ግን አንዲት ሴት ከታች ለሚመጡ ሴቶች አርአያ መሆን ካለባት ሁሉም ነገሮች ሊስተካከሉላት ይገባል፡፡ ሴቶች ወደመሪነት ደረጃ ይምጡ ሲባል፣ ምንድን ነው እንዳትመጣ ያደረጓት ነገሮች የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ነገሮች በዚህ መልኩ ካልተቀረፉ ታችም ያሉ ሴቶች ሞዴል አይኖራቸውም፡፡ ጥቃቅን የሚመስሉት ነገሮችካልተቀረፉ ደግሞ ወደትላልቅ መዘዞች ያመራሉ፡፡ በዚህ ምክንያትመኖሪያቸውን እና ስራቸውን ለመልቀቅ የተገደዱ ሰዎች አሉ፡፡ ለስራ አጥነት ምክንያት ሆነ ማለት ነው፡፡


"ሀኪም በማህበረሰቡ የሚታይበት ቦታው ትልቅ ስለሆነ፡ "ሌሎች ከባባድ ጉዳዮች እያሉ እንዴት ስለዚህ ነገር/ትንኮሳ/ ስሞታ ይቀርባል?" ይባላል፡፡ ግን አንዲት ሴት ከታች ለሚመጡ ሴቶች አርአያ መሆን ካለባት ሁሉም ነገሮች ሊስተካከሉላት ይገባል፡፡ ሴቶች ወደመሪነት ደረጃ ይምጡ ሲባል፣ ምንድን ነው እንዳትመጣ ያደረጓት ነገሮች የሚለውን መመርመር ያስፈልጋል፡፡"  

ሀኪሞች፡- ሌላ በግልሽ የምትሳተፊባቸው ሙያዊ ጉዳዮች ካሉ ብታካፍይን

ዶ/ር አዜብ፡- ማህበረሰቡ ጋር ግንዛቤ መስጠት ከፈለግን አርትን ተጠቅመን ትኩረት መሳብ ይኖርብናል፡፡ አርት እና ሳይካትሪ የሚባል ፕሮጀክት አለ፡፡ ስለዚህ በዚህ ዙሪያ፣ Doctors in Action ከሚባል አማካሪ ተቋም ጋር በመተባበር፣ ተላላፊ ያልሆኑ በሽታዎች ላይ የማህበረሰቡን ግንዛቤ ለመፍጠርእየሞከርን ነው፡፡

ሌላ ደግሞ ከስነልቦና ምክክር፣ ከህግ እና ከተግባቦት ባለሙያዎች ጋር ( Kelela.org) በመሆን በህጻናት ጾታዊ ጥቃት ላይ እንሰራለን፡፡ ጾታዊ ጥቃት የሚያጋጥማቸው ብዙ ህጻናት አሉ፡፡ ስለዚህ ቤተሰብ "እንዴት ነው መከላከል ያለብኝ?" "ልጆቼ ላይ እንዳይደርስ ምን ማድረግ አለብኝ?" "ከደረሰ በኋላስ ምን ማድረግ አለብኝ?" የሚሉትን ነገሮች ስለማያውቅ በአማርኛ ቋንቋዎች መምሪያ አዘጋጅተናል፡፡ በተለያዩ ሀገርኛ ቋንቋዎች ደግሞ ተተርጉሟል፡፡ የሁሉም ሰው ሀላፊነት ስለሆነ ህብረተሰቡም በዚህ ስራ ላይ እንዲሳተፍ እንፈልጋለን፡፡

ማንዴላ ዶክተርስ ደግሞ ማሰልጠን ይፈልጋል፤ ከህክምና ውጪ "ማወቅ፣ ማገዝ፣ ማሰልጠን እፈልጋለሁ" የሚል ሰው ካለ፡፡ ሁላችንም ኔትወርክ ማድረግና መማር ነው የምንፈልገው፡፡ ስለዚህ ብዙ ሰው አብሮን በሰራ ቁጥር እነኚህን ግቦች ይበልጥ ማሳካት እንችላለን፡፡

ሀኪሞች፡- በመጨረሻ ልታስተላልፊ የምትፈልጊው ነገር ካለ

ዶ/ር አዜብ፡- የጤና ስርአት በመንግስት ከፍተኛ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ያም ማለት የሚመደበውን በጀት ማሻሻል፣ የጤና ስአቱን ለማሻሻል፣ የባለሙያዎችን ጥያቄ ማዳመጥ እና መፍትሄ መፈለግ ይኖርበታል፡፡ ይሄ እንዳለ ሆኖ ደግሞ እኛም እንደሀኪም ባለቤትነት ሊሰማን ይገባል፡፡ ችግሩን በጥልቀት የምናቀው እኛው በመሆናችን፣ የመፍትሄ ሀሳቦችም ከኛ ነው የሚፈልቁት ብዬ አስባለሁ፡፡ በተደራጀ እና ግልጽ በሆነ መልኩ፤ የመንግስት ሀላፊዎች ተቀበሉንም አልተቀበሉን፤ የመፍትሄ ሀሳቦችን ማቅረብ አለብን፡፡ በስራ ቦታችን ላይ ማድረግ የምንችለውን በሙሉ እያደርግን ነው ወይ ብለን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ይሄም የመንግስትንም ሆን የማህበረሰቡን አመለካከት ቀና እንዲሆን ያደርገዋል፡፡ ብዙ ተጽእኖዎች ቢኖሩም የህክምና ሙያ ውስጥ ስንገባ የያዝነውን አላማ ሊያደበዝዙብን አይገባም፡፡

ሀኪሞች፡- በጣም እናመሰግናለን!! 

ዶ/ር ደብሩ ጉባ፤ከጭሮዋ አርበረከቴ እስከ ጀርመንዋ ላይፕሲሽ

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Sunday, 16 January 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/