Featured articles

News

13 minutes reading time (2607 words)

ተምረው ስራ ያጡ ሃኪሞች

121733837_3553956954643809_5182254007595472035_n

 እንደመንደርደሪያ፤

በየህክምና ተቋማት የሚስተዋለው የባለሙያ እጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው፡፡ በጤና ተቋማት፣ በጤና ኬላዎችና በሆስፒታሎች ተገኝቶ አገልግሎት ለማግኘት የሚንከራተተው ህዝብም መፍትሄ ሳያገኝ ጊዜን እየተሻገረ ይገኛል፡፡ በተለይ በአሁኑ ወቅት በሃኪሞች እጥረት ሳቢያ በመንግስት ጤና ተቋማት አገልግሎት አሰጣጥ የታካሚዎች መጉላላትና ምሬት በርትቷል፡፡ ችግሩ አገር ያወቀው ብዙዎች የሚስማሙበት በመሆኑም ማስረጃ ማቅረብ አያሻም፡፡

ወዲህ ደግሞ ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ሃኪሞች ስራ ፈት ሆነው ‹‹የስራ ያለህ›› እያሉ ተማጽኖ ላይ ናቸው፡፡ በዘርፉ ‹‹ፍየል ወዲህ ቅዝምዝም ወዲያ›› ይሉ ነገር ሆኗል፡፡ ታካሚንና ሃኪምን ማገናኘትም አልተቻለም:: የባለሙያዎች ቅጥር ለማከናወን የበጀት እጥረት እንደ አንድ ምክንያት የሚገለጽ ሲሆን፤ ጉዳዩ ፈጣን እልባት እንደሚያስፈልገው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ:: ከተለያዩ የትምህርት ተቋማት የተመረቁ ሃኪሞች እንደቀድሞው በህክምና ተቋማት ተመድበው እንዲሰሩ አለመደረጉ አሳሳቢ መሆኑንም ለዝግጅት ክፍላችን ተናግረዋል፡፡

ለሰባት ዓመታት ተምረው ስራ ሳይቀጠሩ በቤተሰብ ላይ መውደቃቸው ከዕለት ዕለት እንደሚያሳስባቸው፣ በዚህ ምክንያትም ለአእምሮ ጤና ችግር፤ ለስነ ልቦና ቀውስ እየዳረጋቸው እንደሚገኝ፣ ለኢኮኖሚ እና ለተለያዩ ችግሮች መጋለጣቸውንም ይናገራሉ፡፡ መፍታት የሚችሉት ችግር እያለ፣ ማገዝ የሚፈልጉት ማህበረሰብ በችግር ላይ ወድቆ ከሰባት ወራት በላይ ስራ ፈትተው መቀመጣቸው በባለሙያዎቹ ላይ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተጽእኖ እንዳለው ይጠቁማሉ፡፡ ከእዚህ ባሻገርም ለማገልገልና ለማገዝ ቃለ መሃላ ፈጽመው ላስተማራቸው መንግስትና ህዝብም ኪሳራ መሆኑንም ይገልጻሉ፡፡

ወደክልሎች የወረደው የቅጥር ስርዓት ለሙስና የተጋለጠ፣ በቋንቋና በተለያዩ ምክንያቶች ሐኪሞችን የገፋ፣ ህሙማንንም ያላገናዘበ እና የናቀ መሆኑን ነው ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚገልጹት፡፡ በመሆኑም ቅጥሩ ወደ ጤና ሚኒስቴር እንዲመለስ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ የማይሆን ከሆነም አቅም እስኪጠናከር ድረስ ስራ የፈቱ ሃኪሞች ወደ ውጭ አገራት ሄደው በሙያቸው በማገልገል በውጭ ምንዛሬ ግኝት አገራቸውን በስራ ዕድል ፈጠራም ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን እንዲያግዙ እንዲደረግ ያመለክታሉ፡፡ ለዚህም ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በአጽንኦት ተመልክተው ፈጣን ዕልባት እንዲሰጧቸው ይጠይቃሉ፡፡

ዝርዝር የቅሬታ አቅራቢዎች አቤቱታ

ከአርባ ምንጭ ዩኒቨርሲቲ በህክምና ዘርፍ የተመረቁት የአዲስ አበባ ከተማው ነዋሪው ዶክተር ያደለው ጌታነህ፤ ቀደም ሲል በማዕከል ደረጃ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ምደባ ይሰጥ ነበረ ሲሉ ያስታውሳሉ:: ነገር ግን ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ ህክምና፣ ራዲዮሎጂ፣ አንስቴዢያና ላብራቶሪ ዘርፍ የተመረቁት ሲመደቡ ሌሎቹ ፈልገው እንዲገቡ ውሳኔ መተላለፉን ይናገራሉ፡፡ ሆኖም ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ እነዚህን ዘርፎች ጨምሮ በህክምናው ዘርፍ ያሉ ተመራቂዎች በሙሉ ራሳቸው ስራ ፈልገው እንዲገቡ መባሉን ነው የሚጠቁሙት፡፡ በተለይም ከጥቅማ ጥቅም ጋር ተያይዞ በህክምና ባለሙያዎች ተነስቶ ከነበረው ተቃውሞና እንቅስቃሴ በኋላ ማንኛውም የጤና ባለሙያ ስራ ፈልጎ እንዲገባ ውሳኔ መተላለፉንም ነው የሚጠቁሙት፡፡

የፌዴራል ጤና ሚኒስቴር ቀድሞ ራሱ ያደርግ የነበረውን ቅጥር በማንሳት ሃላፊነቱን ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች አስተላልፏል ዶክተሩ፤ እነዚህ ሃላፊነቱ የተሰጣቸው አካላት ደግሞ ከፈለጉ ይቀጥራሉ፣ ካልፈለጉም ላይቀጥሩ ይችላሉ፣ ሲቀጥሩም የየራሳቸውን መስፈርት አውጥተው መቅጠር ጀምረዋል ነው የሚሉት፡፡ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በራሳቸው በጀት ልክና ፍላጎት ቅጥር እንዲያከናውኑ ሲደረግ ጭራሽ ቅጥር የማይፈጽሙ እንዳሉም መገንዘብ ይገባ እንደነበረም ይጠቁማሉ፡፡

ትግበራው ሃኪሞች በፈለጉትና ማስታወቂያ በሚወጣበት ቦታ ላይ ተወዳድረው እንዳይቀጠሩ እንቅፋት ፈጥሯል፡፡ ከእዚህ ውስጥም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ፣ በበጀት እጥረትና በተለያዩ ምክንያቶችም ጭራሽ ቅጥር ያላደረጉ ከተማ አስተዳደሮችና ክልሎች አሉ፡፡ አንዳንድ ክልሎች ታዛዥ አለመሆናቸውም ሌላው ችግር ነው፡፡

ጤና ሚኒስቴር የመቅጠር ሃላፊነቱን ለከተማ አስተዳደሮችና ለክልሎች ሲያስተላልፍ ወጥ የሆነ የቅጠር መስፈርት አውጥቶ አለማስተላለፉ፣ የበጀት ጭማሪ አለማድረጉና ሊቀጠሩ የሚገባቸውን የባለሙያ ብዛት አለመጥቀሱ ለችግሩ አባባሽ ምክንያቶች መሆናቸውንም ነው የሚጠቁሙት፡፡ ዞን፣ ከተሞች፣ ክልሎች በየራሳቸው የተለያየ መስፈርት በማውጣት ቅጥር ፈጽመው ባልጀመሩና ስራ ባቋረጡ ባለሙያዎች ምትክ ወይ ከተጠባባቂ አልያም አዲስ ምልመላ አካሂደው ባለሙያዎችን ለማሟላት ጥረት ያላደረጉ ክልሎች መኖራቸውንም ነው ቅሬታ አቅራቢው የሚጠቁሙት፡፡

በክልሎች የሚወጣው ቅጥር ችግር ያለው መሆኑን የሚያነሱት ቅሬታ አቅራቢው፤ ቅጥር በቅርበትና በዝምድና ሆኖ ብልሹ አሰራርና ሙስና ሊፈጠር እንደሚችል፣ በጣም ሩቅና ምቹ ወዳልሆኑ አካባቢዎች ባለሙያዎች ለመስራት ፍቃደኝነት ማጣት ሊያጋጥም እንደሚችሉም ስጋታቸውን ይገልጻሉ፡፡ ቅጥር በማእከል ቢፈጸም ኖሮ ግን ባለሙያው ከምረቃ በኋላ ተመድቦ ሁለት አመት አገልግሎት የመስጠት ግዴታ ሲጥል፤ በአንጻሩ ባለሙያዎችን ፈልጋችሁ ግቡ የሚባለው ነገር ሁሉንም ወደአዲስ አበባና ሌሎች ከተሞች ላይ ብቻ እንዲያተኩሩ ያደርጋል ይላሉ፡፡

ቅጥሩ ከማዕከል ወጥቶ የቅጥር ሃላፊነቱ ለክልሎችና ለከተማ አስተዳደሮች ሲተላለፍ ማዕከሉ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚተገበር የቅጥር መስፈርት ሊያዘጋጅ፣ በጀት ሊመድብ፣ ሊቀጥሩ የሚገባቸውን የባለሙያ ብዛት ተጠቁሞ መተላለፍ ነበረበት ሲሉም ነው የሚያመለክቱት::

‹‹ህክምና በሙያው ጥበብ ነው፡፡ ሙያውን በየጊዜው እያሳደግነው የምንሄደው እንጂ በአንዴ የምናዳብረው አይደለም፡፡ ካልሰራንበት አንድም ይጠፋል፣ ተጽእኖውም ከባድ ነው›› ይላሉ፡፡ አንድ ወላጅ ለልጁ ሃኪም ደረጃ እስኪደርስ ለማስተማር ሰባት ዓመታት የሚያወጣውን የኢኮኖሚክስ ወይም ሌላ ሙያ ላይ ለሶስትና አራት ዓመታት ከሚያስተምር ወላጅ ጋር ስታነጻጽር ችግሩ ይገባሃል፡፡ አንድ ልጁን ህክምና ለማስተማር ገንዘቡን የሚያወጣ ወላጅ ለሁለት ልጁ የሚሆን ሃብት ነው የሚያባክነው፡፡ ይህ ኢኮኖሚያዊ ጫናው ትልቅ ነው፣ በስነ ልቦናም የሚያደርሰው ተጽእኖ ከባድ ነው፡፡ ለአንድ ሃኪም ተምሮ ስራ አጥቶ መቀመጥ የበለጠ ከባድ ነው፡፡ ያዳበርነውን ዕውቀት እያጣ ነው የምንሄደው ሲሉም ኪሳራውን ይጠቅሳሉ፡፡

በየጤና ጣቢያው የባለሙያ እጥረት ባለበት፣ በተለይም በአለም አቀፍም ሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስ በተስፋፋበት አጋጣሚ የህክምና ባለሙያዎች በስራ ማጣት መንገላታታችን መንግስት የጤናውን ዘርፍ ቸል ማለቱንና የተሰጠው ግምት አነስተኛ መሆኑን የሚያሳይ ነው ሲሉም ይወቅሳሉ፡፡ ትኩረት ቢሰጠው ኖሮ ለሰባት ዓመታት የተማሩ የህክምና ባለሙያዎች በየቦታው እንድንበተንና እንድንገላታ አይደረግም ነበር ይላሉ፡፡

ቀደም ሲል በአገር አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ የህክምና ባለሙያዎች እጥረት እንደነበር በማስታወስም፤ ችግሩን ለመቅረፍ በርካታ ቁጥር ያላቸው በዘርፉ ሰልጥነው ዘርፉን እንዲቀላቀሉ መንግስት መወሰኑን ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ትኩረት የተሰጠው ማስተማሩን ብቻ እንጂ ከምርቃት በኋላ ተመራቂዎች ወደ ስራ ስለሚሰማሩበት፣ ምን ያክል በጀት እንደሚያስፈልግ ቀድሞ ዝግጅት አለመደረጉና በእቅዱም አለመካተቱ ችግሩ እንዲፈጠር ማድረጉን ነው የሚጠቅሱት፡፡ ‹‹አሁን አቅርቦትንና ፍላጎትን የማጣጣም ችግር አጋጥሟቸዋል፣ ባለሙያውም ዘርፉ ከሚይዘው መደብ በላይ ሆኖባቸዋል›› ባይ ናቸው ዶክተሩ፡፡

ከሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ በህክምና የተመረቁት የሐዋሳ ከተማ ነዋሪው ዶክተር በእሱፍቃድ ተስፉ፤ ላለፉት ሰባት ወራት ስራ አለመጀመራቸው የጤና ሚኒስቴር እንደቀድሞ ለተመራቂ ሃኪሞች ምደባ አለማድረጉ ለችግሩ መፈጠር ምክንያት መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡

ሚኒስቴሩ የቅጥር ሃላፊነቱን ለክልሎች ማስተላለፉ ትክክል እንዳልሆነ የሚጠቁሙት ቅሬታ አቅራቢው፤ ያገኙትን አጋጣሚ በመጠቀም አንዳንድ ክልሎች ከአማርኛ ቋንቋ በተጨማሪ የአካባቢያቸውን ቋንቋ የሚችል መሆን እንዳለበት በቅጥር ማስታወቂያ መስፈርቱ ማካተታቸውንና ሂደቱም ቅጥር ለማግኘት እንዳስቸገራቸውም ነው የሚገልጹት፡፡

ከመጀመሪያ አመት አንስቶ ለልምምድ እስኪመደቡ እስከ ሰኔ ወር 2011 ዓ.ም የስራ ምደባ ይሰጥ የነበረው ጤና ሚኒስቴር እንደነበር በመጠቆም በስልጠና ወቅት አሰራሩ እንደሚቀየር ምንም አይነት መረጃ እንዳልተሰጣቸውም ያመለክታሉ፡፡ ችግሩ የተከሰተው በሃኪሞች ተነስቶ ከነበረው ተቃውሞ በኋላ ሲሆን፤ የገጠመውን የበጀት ችግር ከመፍታት ይልቅ ሃላፊነቱን ለመሸሽ የተደረገ ሁኔታ ነው ይላሉ፡፡

እንደ አገር የትኛውም የግልና የመንግስት ተቋም የታካሚዎች ቁጥር ሲታይ ብዙ መሆኑን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ ‹‹ህዝቡ በጤና ተቋማት ቀርቦ ለመታከም ወረፋ አልደርስ ብሎት በህክምና ዕጦት እየተሰቃየ ይገኛል፡፡ ታካሚንና ሃኪምን ማገናኘት አልተቻለም፡፡ በጀት የለም በሚል ተልካሻ ምክንያት በርካታ ባለሙያዎች በቤታችን ተቀምጠን በአንጻሩ ታካሚ መንገላታቱ የማይገባ ድርጊት ነው›› ይላሉ፡፡

በርካታ በሽተኞች የህክምና እርዳታ ሳያገኙ በህክምና ማጣት እየተሰቃዩ፣ ለሞት እየተዳረጉም ይገኛሉ፡፡ በቀላሉ መፍታት የሚቻለውን ነገር ችላ በመባሉ ችግሩ አይሏል ይላሉ፡፡ ‹‹ለሰባት ዓመታት ተምረን ስራ ባለመቀጠራችን በቤተሰብ ላይ ወድቀን ጫና ለመፍጠር ተገድደናል፣ ለአእምሯዊ ጤና መቃወስ፤ ለስነ ልቦና፣ ለኢኮኖሚ እና ለተለያዩ ችግሮች እየተጋለጥን እንገኛለን›› ይላሉ፡፡ መፍታት የሚችሉት ችግር እያለ፣ ማገዝ የሚፈልጉት ማህበረሰብ በችግር ላይ ወድቆ ሳለ ስራ ፈትተው መቀመጣቸው በባለሙያዎቹ ላይ ከሚፈጥረው ተጽእኖ ባሻገር ለማገልገልና ለማገዝ ላስተማራቸው መንግስትና ህዝብም ኪሳራ መሆኑንም ነው ሃኪሙ የሚገልጹት፡፡

ቅጥር ለማግኘት የሐዋሳ ከተማ ጤና መምሪያን በተደጋጋሚ እንደጠየቁ የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢው፤ የቅጥር ማስታወቂያ እናወጣለን ጠብቁ የሚል ምላሽ ቢሰጣቸውም የቅጥር ማስታወቂያ ሊወጣ አለመቻሉንም ነው የሚናገሩት፡፡ የደቡብ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች እንዲሁም የሲዳማ ክልል ጤና ቢሮ የሚገኘው በሐዋሳ ከተማ እንደ መሆኑ ቀርበው መጠየቃቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ የደቡብ ክልል የቅጥር ስልጣኑን ለዞኖች መስጠቱንና ቅጥር ማቆሙን እንደገለጸላቸው ይናገራሉ:: በዞን ሄደው ለማናገር ደግሞ የዞኑን ቋንቋ ለሚናገሩ ቅድሚያ ተሰጥቶ እንደሚቀጠሩና እርሳቸውና ሌሎች ጓደኞቻቸው ግን ስራ አጥተው ቤት መቀመጣቸውን ይናገራሉ፡፡ ሁኔታውን በመገንዘብ የሚመለከታቸው አካላት ስራ ተመድበው ህብረተሰቡን እንዲያገለግሉ እንዲያደርጉላቸው ይጠይቃሉ፡፡

ከባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ በህክምና ትምህርት የተመረቁት ዶክተር ገደፋው ክንዱ፤ ከ2011 ዓ.ም በፊት ሃኪሞችን ይመድብ የነበረው ጤና ሚኒስቴር እንደነበር ይጠቅሳሉ፡፡ ሆኖም ግን ከተጠቀሰው ጊዜ አንስቶ ሚኒስቴሩ ሃላፊነቱን ከእራሱ በማንሳት ለክልል እና ለከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮዎች ሃላፊነት መስጠቱን ይናገራሉ፡፡ ግን የጤና ሚኒስቴር በየዓመቱ ሃላፊነቱን ሲያስተላለፍ በተለይም የበጀት ችግር እንዳይገጥም በየአመቱ እየተመረቁ የሚወጡ ጠቅላላ ሃኪሞችን መሰረት በማድረግ በክልሎች ጤና ተቋማት ላይ ሊደርስ የሚችለውን የበጀት ችግር ለመሸፈን ቃል ገብቶ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡ ነገር ግን ጤና ሚኒስቴሩ እያደረገ ያለው ቃል በገባው መሰረት በየአመቱ የሚመረቀውን ጠቅላላ ሃኪም ያገናዘበ አይደለም ሲሉ ነው የሚገልጹት፡፡

በጤናው ዘርፍ የሚታዩ በርካታ ችግሮች መፍትሄ እንዲሰጣቸው የሚጠይቅ በአገር አቀፍ ደረጃ ተቃውሞ ተነስቶ እንደነበር ዶክተሩ ያስታውሱና፤ ውሳኔው ሃላፊነትን የመሸሽ መሆኑንም ይናገራሉ፡፡ ሃኪሞች ላነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ ከመስጠት ይልቅ ለመሸሽ ተብሎ የተደረገ ሊሆን ይችላል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸውም ይናገራሉ፡፡ የደመወዝ፣ የጥቅማ ጥቅም ማስተካከያ ጥያቄ፣ የህክምና ተቋማት ላይ የሚስተዋል የመድሃኒትና የላቦራቶሪ እጥረት፣ የህሙማን መጉላላት

ጉዳይ በቅሬታ ተነስቶ እንደነበረም ያክላሉ፡፡

ቅጥሩ ወደ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ሲወርድ ቋንቋንና የትውልድ ሰፈርን መሰረት ያደረገ ቅጥር እንዲቀጠር ምክንያት እንደሆነ፣ አንዳንድ አካባቢዎች ደግሞ የክልሉን/ የአካባቢውን ቋንቋ የማያውቅ ለመቅጠር ችግር ይፈጥራል ሲሉም ነው የሚናገሩት፡፡ በአንዳንድ የዞን ጤና መምሪያዎች የሚደረገው ቅጥርም በቋንቋ ሽፋን ለሙስና የተጋለጠ መሆኑንም ነው የተናገሩት:: አፋር፣ ትግራይና ሶማሌ ክልሎች ጭራሽ ቅጥር እንዳልፈጸሙ ፣ በአማራ ክልልም የበጀት ችግር መኖሩ እንደተገለጸላቸውም ነው የሚናገሩት፡፡

ከፍተኛ መስዋእትነት ከፍለን በህክምና ለሰባት ዓመታት ተምረን ጨርሰን ቤት ውስጥ መቀመጣችን ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ይህንን ያህል የተማረ ሃኪም በየቤቱ እንዲቀመጥ ተፈርዶ በየህክምና ተቋማት በርካታ ህሙማን በሃኪም እጥረት እየተንገላቱ ናቸው፡፡ በአንድና በሁለት ቀናት መፍትሄ ማግኘት እየቻሉ በየጤና ተቋሙ ሲጉላሉ የሚሰነብቱ በርካታ ህሙማን መሆናቸውን መታዘባቸውንም ይገልጻሉ፡፡

ችግሩ ዘርፈ ብዙና ያልተስተዋለ መሆኑን ነው ዶክተር ገደፋው የሚናገሩት፡፡ በየጤና ተቋማቱ ባለው የሃኪሞች እጥረት ምክንያት ወሩን ሙሉ በተረኝነት የሚገቡ ባለሙያዎች መኖራቸውንም ይጠቁማሉ፡፡ በእዚህ ሁኔታ 30 ቀናት ሙሉ እንቅልፍ አይተኙም፣ አንድ ባለሙያ በሚሰጠው ህክምና ተገልጋይ እርካታ ያገኛል ለማለት ያስቸግራል ሲሉም ይጠቁማሉ፡፡

መንግስት፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የጤና ተቋማት የጤናውን ዘርፍ ረስተውታል ሲሉ ይወቅሳሉ። ሰባት አመታት ለደከሙ ባለሙያዎች ሞራልን የሚነካ፣ ለአገር ኪሳራን በማድረስና መጥፎ ገጽታን በማላበስ የህክምና ትምህርት እንዲጠላ የሚያደርግ መሆኑንም ነው የሚገልጹት፡፡

በኦሮሚያ ክልል እና አንዳንድ አካባቢዎች የሚገለጸው ነገር የቋንቋ ክፍተት በህክምና አሰጣጥ ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል የሚል ምክንያት እንደሚነሳ ዶክተር ገደፋው ጠቁመውም፤ ጉዳዩ ከእዚህ በፊት ተነስቶ የማያውቅ፣ በተለያዩ ክልሎች ተሰማርተው አገልግሎት የሰጡና እየሰጡ የሚገኙ ሐኪሞች ይህ ችግር ገጥሟቸው የማያውቅና ሲሰራበት የኖረ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ቋንቋችንን የማያውቁ በርካታ የውጭ አገር ሃኪሞች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው አገልግሎት እንደሚሰጡና ኢትዮጵያውያንም ቋንቋን ወደማያውቁባቸው ወደ ተለያዩ የአለም አገራት ለህክምና እንደሚጓዙ፣ አገልግሎት እንደሚያገኙና እንደሚሰጡም ነው የሚጠቁሙት:: ቋንቋ ለዘርፉ ችግር አይደለም፤ ለቅጥር ቋንቋን እንደ መስፈርት መወሰኑም መፍትሄ አይደለም ይላሉ ዶክተር ገደፋው፡፡

በመሆኑም በፍጥነት እንዲቀጠሩ ይጠይቃሉ፡፡ ሆኖም ይላሉ ቅሬታ አቅራቢው ‹‹ባሉ የተለያዩ ችግሮች በአገር ውስጥ ቅጥር ለመፈጸም የሚቸገሩ ከሆኑ ከተለያዩ የአፍሪካ አገራትና የአረብ አገራት ኢትዮጵያውያን ሃኪሞችን ለመቅጠር የጤና ሚኒስቴርን በጠየቁት መሰረት ተፈቅዶልን የወጪ መጋራትን በመክፈል ወጥተን ለመስራት ይፈቀድልን›› ይላሉ፡፡

እንዲወሰንላቸው የሚጠይቁት

ጉዳዩ እልባት እንዲያገኝ በማሰብ ይመለከታቸዋል ያልናቸውን አካላት ጠይቀናል የሚሉት ቅሬታ አቅራቢዎች፤ ችግሩን ጤና ሚኒስቴር፣ አዲስ አበባ ጤና ቢሮ፣ አማራ ክልል ጤና ቢሮ፣ የኢትዮጵያ ህክምና ማህበርና የአማራ ሃኪሞች ማህበር በተገቢው መንገድ ያውቁታል ሲሉ ነው የሚጠቅሱት፡፡

ሆኖም ግን ጉዳዩ እልባት ሊሰጠው እንዳልቻለ ይናገራሉ፡፡ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት አዲስ የተተገበረውን የቅጥር ሁኔታ በመቀየር ወደ ማዕከል (ወደጤና ሚኒስቴር) መመለስ ይኖርበታል፡፡ ይህ ካልሆነ ጤና ሚኒስቴር ለቀጣሪዎቹ የቅጥር መስፈርት አውጥቶ እንዲተገበር ማስተላለፍ ይጠበቅበታል፡፡ ቀጣሪዎችም በየጊዜው ሊቀጠሩ የሚገባቸውን የባለሙያዎች ብዛት ማመላከት ይኖርበታል፡፡ ለዘርፉ ትኩረት በመስጠትም የበጀት ድጎማ ሊደርግ ይገባዋል፡፡

ጤና ሚኒስቴሩ ይሄንን ለማድረግ አቅሙ የማይችል ከሆነ ግን ችግሩን ለመቅረፍ ሌላ የመጨረሻ አማራጭ አለን ባይ ናቸው ምሩቃኑ፡፡ የኢትዮጵያን መንግስት ሃኪሞች እንዲሰጡት የጠየቁ የውጭ አገራት መኖራቸውን ያመለክቱና፤ ‹‹ተመርቀን ቤት ከምንቀመጥ መንግስትን ወደ ጠየቁ የውጭ አገራት ሄደን የምናገለግልበት ሁኔታ ሊመቻችልን ይገባል›› ነው የሚሉት፡፡

ይህ መሆኑ አንድም ልምድ አዳብረው ለመመለስ እንደሚያስችላቸው፣ ለአገሪቱም የውጭ ምንዛሬ እንደሚያስገኙና ካጋጠማቸው የሥራ ማጣት ችግርም መፍትሄ እንደሚሆናቸው ይጠቁማሉ፡፡ ከሌሎቹ አማራጮች ወደ ውጭ አገራት ሄደው ቢሰሩ የተሻለ መሆኑን በመጠቆምም በአማራጩ ላይ ትኩረት በማድረግ እልባት እንዲሰጠውም ይጠይቃሉ፡፡

አማራ ክልል ላይ በየሆስፒታሉ ተመድበው የነበሩ ሃኪሞች የቅጥር ውል ከፈጸሙ በኋላ መደቡን ትተው ሄደዋል፡፡ የእነዚህ ሃኪሞች በጀት የተለቀቀ ቢሆንም የየሆስፒታሉ አስተዳዳሪዎች ሃኪሞቹ እንደለቀቁ ለጤና ቢሮ ሪፖርት አላደረጉም ሲሉ ይናገራሉ፡፡ ቅጥር ሊፈጸም ሲገባው ጥለው የሄዱ ባለሙያዎች እንዳልተተካና በእዚህ ምክንያትም በየአመቱ ከ15 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚባክን ነው የሚያመለክቱት፡፡ ይህ ገንዘብ እየባከነ ነው፣ ሃኪሞችም ስራ አጥተን ተቀምጠናል፣ ህሙማንም ሃኪም አጥተው እየተንገላቱ ናቸው ይላሉ፡፡

የኢትዮጵያ ህክምና ማህበር

የማህበሩ ፕሬዚዳንት ዶክተር ተግባር ይግዛው፤ ጉዳዩን ማህበሩም እንደሚያውቀውና አንገብጋቢ ችግር መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡ ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ጋር ሲነጻጸርም ሆነ ዘላቂ የልማት ግቦችን ከማሳካት፣ ሁሉን አቀፍ የማህበረሰብ ጤና ለማህበረሰቡ ለማዳረስና የህዝቡን የጤና ሁኔታ ከማሻሻል አንጻር የሚያስፈልጓት የጤና ባለሙያዎች የሏትም ወይም ቁጥራቸው ዝቅተኛ ነው ይላሉ፡፡

በኢትዮጵያ የሃኪሞች ቁጥር ከሕዝብ ቁጥር ጋር ሲነጻጸር አንድ ሃኪም በአማካኝ የሚደርሰው ለ10 ሺህ ሰዎች ነው፡፡ አፍሪካ ውስጥ ስንመለከት ግን ከህዝብ ቁጥር ጋር ያለው ጥምርታ ሶስት ይሆናል፡፡ የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት የአለም ጤና ድርጅት ያወጣውን ቁጥር ብንመለከት ለአንድ ሺ ሰዎች አራት የሚደርሱ ዶክተሮች፣ ነርስና ሚድዋይፈሪዎች ያስፈልጋሉ ተብሎ ይገመታል:: የተቀመጡትን ዘላቂ የጤና የልማት ግቦችን ኢትዮጵያ እንድታሳካ አሁን ያለው የሃኪም፣ የነርስና የሚድዋይፈሪ ቁጥርን በእጥፍ መጨመር ይገባል፡፡ በመሆኑም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የሆነ የጤና ባለሙያና የሃኪም እጥረት አለ ይላሉ ዶክተር ተግባር፡፡

እንደፕሬዚዳንቱ ማብራሪያ፤ መንግስት ከአገር ውስጥ ሃብት በየአመቱ ለጤና የሚመድበው ከአምስት በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህ መጠን በአለም አቀፍ ከሚመደበው 10 በመቶ አማካኝ ጋር ሲነጸር አነስተኛ ነው፡፡ ለችግሩ አንዱ መሰረታዊ ማነቆ ገንዘብ ነው:: ለጤና ዘርፉ በቂ ገንዘብ ከተመደበ በጀቱ በርካታ ባለሙያዎችን ለመቅጠር ይውላል፡፡ በመሆኑም መንግስት ለጤና ዘርፉ የሚመድበውን በጀት መመልከት ይኖርበታል፡፡

ይህ ሆኖ ሳለ በአሁኑ ወቅት ከ500 በላይ የሚሆኑ ሃኪሞችና በርካታ ነርሶች ስራ የላቸውም፡፡ ስራ ቢይዙ የበርካታ ማህበረሰብን የጤና ችግር ይፈታሉ የምንላቸው ባለሙያዎች ስራ አጥ ሆነው ተቀምጠዋል፡፡ እጥረት እያለ፣ ለዘርፉ እንደሚያስፈልጉ እየታወቀና ለሰባት አመታት ያህል የተማሩ፣ አገሪቱም ከፍተኛ ወጪ ያወጣችባቸው ባለሙያዎች መቅጠር ያልተቻለባቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ ሆኖም ዋናው ምክንያት ግን የጤና ተቋማትና ጤና ቢሮዎችን ለመቅጠር በቂ መደብና በጀት አለመያዛቸው ለመቅጠር ያላስቻላቸው ምክንያት ነው ባይ ናቸው ዶክተሩ፡፡

ከበጀትና ከመደብ ውስንነቱ ባሻገር ለመቅጠር እየቻሉ ያላደረጉም አሉ ሲሉም ይታዘባሉ፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ጤና ሚኒስቴር ለድህረ ምረቃ ለ100 ሃኪሞች ደመወዝ እንደሚከፍልና በእነርሱ ምትክ እንዲቀጥሩ ከጤና ቢሮዎች ጋር ስምምነት መደረጉን በማስታወስም፤ የጤና ቢሮዎች ግን የድህረ ምረቃ ትምህርት ለመማር መደቡን በሚለቁ ባለሙያዎች ምትክ እየቀጠሩ አይደለም ሲሉ ነው የሚታዘቡት፡፡ የተወሰኑ የቀጠሩ ቢኖሩም ያልቀጠሩ የተወሰኑ ቢሮዎች መኖራቸውንም ያክላሉ፡፡

ተግባራዊ ከተደረገው የፌዴራሊዝም ስርዓትም አንጻር የሰዎች ቅጥር ላይ ክልሎች የአካባቢውን ቋንቋ ተናጋሪ ለሆነ የአካባቢው ሰው ቅድሚያ መስጠታቸው ችግር የለውም፣ ቋንቋውን የሚያውቁ የተሻለ የጤና አገልግሎት ይሰጣሉ ተብሎ መታሰቡም ስህተት አይደለም የሚሉት ዶክተር ተግባር፤ ነገር ግን የአካባቢ ተወላጅ ካልሆንክ ወይም የአካባቢውን ቋንቋ ካልቻልክ የህክምና አገልግሎት መስጠት አትችልም ብሎ ማሰብ ልክ አይደለም ይላሉ፡፡

ዘመናዊ ህክምና አገር ውስጥ የገባው በሩሲያውያኖች በመሆኑ ያኔ ያገዙን ቋንቋችንንም ሆነ ባህላችንን የማያውቁ ናቸው ይላሉ፡፡ ህክምና አለማቀፋዊ መሆኑንም ያመለክታሉ፡፡ በርካታ ኢትዮጵያውያን ባላደጉበት ባህል ወደተለያዩ የአለም አገራት ተጉዘው በሙያቸው እየሰሩ እንደሚገኙም አብነት ይጠቅሳሉ:: ስለዚህ ባለሙያዎቹ የሚሰሩበትን ማህበረሰብ ስነ ልቦና ማወቅ፣ ቋንቋውን መልመድ፣ የማህበረሰቡን ፍላጎት ተረድተው ጥራት ያለው አገልግሎት እንዲሰጡ መደረግ ነው ያለበት እንጂ ቋንቋውን ስለማታውቀው ወይም ከአካባቢው ስላልወጣህ አታገለግልም ማለት ግን የማህበረሰቡን የጤና አገልግሎት የማግኘት ዕድልን እንደመከልከል እንደሚቆጠር ነው የሚገልጹት፡፡

አዝማሚያዎቹ የቆዩ ቢሆንም በተለይ ከቅርብ አመታት ወዲህ ችግሮቹ እየጨመሩ መሆናቸውንና በጤና ሚኒስቴር የተመደቡም የሚመለሱበት ሁኔታ መኖሩንም ይናገራሉ፡፡ እንደዚህ አይነት ሁኔታዎች ለአገሪቱ የጤና ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑንም ይጠቁማሉ:: የአካባቢውን ባህልና ቋንቋ እየለመዱ፣ በጋብቻ ተጣምረው ልጆች አፍርተው እየኖሩ የሚገኙ በህክምና ብቻ ሳይሆን በመምህርነትና በሌሎች ሙያዎች መኖራቸውንም ይጠቅሳሉ፡፡ ቋንቋውንና ባህሉን እንዲያውቁት ማስተማር የህብረተሰቡን ስነ ልቦና እንዲገነዘቡት ማበረታታት ተገቢ ነው፤ ግን እስካለመቅጠር ደረጃ መደረስ የለበትም፡፡ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮችም ለትግበራው ተባባሪ መሆን አለባቸው ይላሉ፡፡

ዶክተር ተግባር ወጥ መስፈርት ይውጣ የሚለውን ሃሳብ አይስማሙበትም፡፡ ክልል ጤና ቢሮዎች ከተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በክልላቸው ስለሚከናወነው ነገር ወሳኞች መሆናቸውን ያነሳሉ:: ይህንን አድርጉ መባልም የለባቸው ይላሉ፡፡ ህክምና አለምአቀፋዊና በርካታ ኢትዮጵያውያን ሃኪሞች ወደተለያዩ የአለም አገራት ተንቀሳቅሰው እየሰሩ የሚገኙበት ሙያ መሆኑን ይናገራሉ፡፡

ሃኪሞቹ ቅጥር ወደጠየቁ የውጭ አገራት ቢላኩስ?

ከተለያዩ ተቋማት የተመረቁ ሃኪሞች ስራ ካጡ ጊዜ አንስቶ ውይይት እያደረግን እንገኛለን ይላሉ ዶክተር ተግባር፡፡ በመንግስት ላይ ጫና በማሳደር ለችግሩ አማራጭ ናቸው የምንላቸውን መፍትሄዎች ለመጠቆም እየሞከርን ነው፡፡ ከጤና ሚኒስቴር ጋርም ውይይት እያደረግን እንገኛለን ሲሉም ያክላሉ፡፡

የተማሩ፣ የሰለጠኑ ባለሙያዎችን መንግስት ከመንግስት ጋር በሚደረግ ስምምነት ሄደው እንዲሰሩ ቢደረግ ለዜጎች የስራ ዕድል እንደሚፈጥር፣ ጥሩ ገቢ እንዲያገኙ እንደሚያስችል፣ ለውጭ ምንዛሬ ግኝት የበኩላቸውን ሊወጡ እንደሚያስችል ይጠቁማሉ፡፡የአገር ኢኮኖሚ ውስን ከመሆኑ አንጻርም መንግስት ላይ የስራ ዕድል ፍጠር በሚል የሚደረገውን ጫናም ይቀንሳል ይላሉ፡፡

የእኛ ምኞት ይህ እንደ መጨረሻ አማራጭ እንዲሆን ማድረግ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ዝቅተኛ ባለሙያ ባለበት አገር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ የአገር ውስጥ በጀትን ከፍ በማድረግ፣ መደቦች እንዲፈጠሩ ማድረግና የግል የጤና ዘርፉን በማሳደግ የህብረተሰቡን ጤና ለመጠበቅ እንችላለን ህይወት እናድናለን፡፡ ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባም ይሄ ነው፡፡ ያለው ተጨባጭ እውነታ ይህንን ካልፈቀደ ግን፤ በሌላ ቦታ ላይ ስራ እያለ እዚህ መሆን አለባችሁ ተብለው መያዝ የለባቸውም፡፡ ቅድሚያ የሚሰጠው ባይሆንም ይሄም እንደ አንድ አማራጭ መታሰብ ይኖርበታል፡፡

ምን መደረግ ይኖርበታል ?

እንደ ዶክተር ተግባር እሳቤ ከሆነ በቂ ሃኪሞችና የጤና ባለሙያዎች አለመኖራቸውን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ አስፈላጊ የጤና ባለሙያዎችን ለመቅጠር መንግስት ለጤናው ዘርፍ የሚበጅተውን መጠን መጨመር ይኖርበታል፡፡ ለጤና ዘርፉ የሚመድበውን በጀት መመልክት አለበት ይላሉ፡፡ ጊዜው ያለፈበት፣ ካለው የስራ ጫና እና ከህብረተሰቡ ፍላጎት ጋር የማይመጣጠን የመደብ ሁኔታን በጥናት ላይ ተመስርቶ መቀየር እንደሚያስፈልግም ነው የሚያመለክቱት፡፡

ለአንድ ጠቅላላ ሆስፒታል፣ ለመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ሆስፒታሎችንም ያማከለ የባለሙያ ምደባ ሊደረግ ይገባል፡፡ አቅም በፈቀደና ማሰልጠን እስከተቻለ ድረስ ወደጤና ጣቢያዎች ባለሙያዎችን በርካታ ሃኪሞችን መቅጠር ያስፈልጋል፡፡

በኢትዮጵያ አብዛኛውን ቅጥር የሚሸፍነው መንግስት ነው፡፡ የመንግስት የመቅጠር አቅም እየደከመ ሲሄድ ተመራቂ ሃኪሞች ስራ ያጣሉ፡፡ በመሆኑም በጤና ገበያው የግል ዘርፉ ያለውን ድርሻ ማጎልበት ይገባል፡፡ የግል ዘርፉ አቅም እንዲጎለብት መደረጉ ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ማዳረስ ይቻላል፡፡ ለበርካታ የጤና ባለሙያዎችም የስራ ዕድል መፍጠር ያስፈልጋል:: አሁን ከ80 በመቶ በላይ ተመራቂዎችን የሚቀጥረው መንግስት ነው፡፡ እንደኬንያ ያሉ ጎረቤት አገሮችን ጨምሮ የጤና ባለሙያዎች የሚቀጠሩት በግል ዘርፉ ነው፡፡ የግል ጤና ዘርፉን በማሳደግ ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው አገልግሎት ከማዳረስ ባሻገር ለሃኪሞችና የጤና ባለሙያዎች የስራ ፈጣሪነት ድርሻውን እንዲወጣ ማስቻል ይገባል፡፡

የክልል ጤና ቢሮዎች፣ የጤና ሚኒስቴር፣ የህክምና ማህበራት በጉዳዩ ዙሪያ የሚሳተፉበት የውይይት መድረክ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡ አንድ የጤና ባለሙያ የአካባቢው ቋንቋ ተናጋሪ አለመሆን ወይም በአካባቢው አለመወለዱ ምክንያት መሆን የለበትም፡፡ ትግበራው ማንንም አይጠቅምም፡፡ ማህበረሰቡ አገልግሎት ሳያገኝ ይቀራል፤ ባለሙያውም ስራ ማግኘት እየቻለ ስራ አጥ ይሆናል፡፡ በአገርም ላይ ኪሳራ ይደርሳል፡፡

ጤና ሚኒስቴር

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ እንዲሰጠን የሚመለከተውን አካል በስልክ ጠይቀናል፡፡ የስራ መደራረቦች በመኖራቸው በሌላ ጊዜ ቀጠሮ እንደሚይዙልን ቃል ገብተዋል፡፡ ሚኒስቴሩ በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት ፍቃደኛ ከሆነ ዝግጅት ክፍሉ የሚያስተናግደው ይሆናል፡፡

አዲስ ዘመን ጥቅምት 4/2013

source

Interview of Dr. Melkamu Meaza on Medico-legal is...
Women Surgeons’ Experiences of Interprofessional W...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Tuesday, 16 August 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/