ኮሮናቫይረስ፡ ኢንሹራንስና ቤት ለኮሮናቫይረስ ጤና አገልግሎት ሰጪዎች

 የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋትን ለመቀነስ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ወይም ከህመምተኞች መራቅ ለጤና ባለሙያዎች አማራጭ አይደለም።


በብዙ አገራት እየሆነ እንዳለው በኢትዮጵያም የጤና ባለሙያዎችም ሆነ በቀጥታ ከህሙማኑ ጋር የሚሰሩ ሰዎች ምርመራ ማድረግ፣ በአምቡላንስ መውሰድ፣ ለህመምተኞቹ ድጋፍና ምቾትን እንዲሁም መድኃኒትን ከማዘዝ ጀምሮ ለብዙዎች ስጋት የሆነውን ቫይረስ በቀጥታ እየተጋፈጡት ይገኛሉ።

በዚህም ምክንያት በርካታ የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ህይወታቸው አደጋ ውስጥ ገብቷል።

ከሰሞኑም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ ድጋፍ ሰጪ አካላትም ሆነ የጤና ባለሙያዎች በኢንሹራንስ እንዲሸፈኑ ውሳኔ ላይ ደርሷል።

ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ ህይወታቸውን አደጋ ላይ ጥለው ወረርሽኙን ለመቆጣጠር እየሰሩ ያሉ ባለሙያዎኞች ለስድስት ወር ያህል የኢንሹራንስ ሽፋን ለመስጠት ስምምነት ላይ መደረሱን የጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ አስታውቀዋል።

ኢንሹራንሱ ዶክተሮችና ነርሶችን ብቻ ሳይሆን በፅዳት ላይ የተሰማሩ፣ የአምቡላንስ አሽከርካሪዎች ወይም ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር በቀጥታ የሚሰሩ ሠራተኞችን በሙሉ ይመለከታል።

"ቫይረሱ ለጤና ባለሙያዎች ብቻ ሳይሆን በሌላ ሥራ ለተሰማሩት እንደ ፅዳት ወይም የአምቡላንስ ሾፌሮች ስጋት ሆኗል። ለበሽታውም ተጋላጭ ናቸው። በዚህ ምክንያት በሽታው ቢይዛቸውና ህይወታቸው አደጋ ላይ ቢወድቅ ምን መሆን አለበት? የሚለውን ታሳቢ በማድግ ነው የኢንሹራንስ ስፋን እንዲያገኙ የተወሰነው" ብለዋል ሚኒስትሯ ለቢቢሲ።

ይህንን የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጠው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት እንደሆነና አገልግሎቱን ያቀረበው በነፃ እንደሆነና ሃሳቡም ከእራሱ ከድርጅቱ የመጣ መሆኑን ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም ሌሎች ለመደገፍ ፍላጎት ያላቸው የኢንሹራንስ አገልግሎት ሰጪዎች ጋርም ውይይት መጀመሩን ያመላከቱት ሚኒስትሯ መንግሥትም ሰፋ ባለ መንገድ የኢንሹራንስ ሽፋን የሚሰጥበትን መንገድ እየቀየሰ መሆኑን ተናግረዋል።

ከኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የሚሰሩ የጤና ባለሙያዎችም ሆነ ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞች ቁጥር በየጊዜው የሚለዋወጥና እየጨመረ የሚሄድ ከመሆኑ አንፃር የኢንሹራንሱ ሽፋንም ሆነ የመኖሪያ ቤት የሚያገኙ ሰዎችን ቁጥር በትክክል መናገር ከባድ እንደሆነም ገልፀዋል።

ዶክትር ሊያ እንደሚሉት በአገሪቱ ውስጥ የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመቆጣጠር በሺህዎች የሚቆጠሩ ሠራተኞች ተሰማርተዋል፤ በዚህ ዓመት እንኳን አዲስ የተቀጠሩ 3800 ባለሙያዎች አሉ። ኢንሹራንስ ሽፋኑም እነዚህን ጨምሮ ለወደፊቱ የሚቀጠሩትንም የሚያካትት ይሆናል።

ከኢንሹራንስም በተጨማሪ የኮቪድ-19 ህክምና በሚሰጥባቸው ማዕከላት ቀጥታ ፈጣን ምላሽ እየሰጡ ያሉ የጤና ባለሙያዎች ወደየቤታቸው መመላለሱ ስጋት በመፍጠሩ ከዚህ ስጋት ነፃ ሆነው የሚሰሩበትም ሁኔታ ለማመቻቸት ቤቶች እንዲሰጣቸው መወሰኑን አመልክተዋለወ።

አንዳንድ ሆስፒታሎች በተለይም ማስተማሪያ ያላቸው ተቋማት ተማሪዎች ይጠቀሙባቸው የነበሩ ዶርሚተሪዎች (የማደሪያ ክፍሎች) ተማሪዎቹ በአሁኑ ወቅት ስለሌሉ ለዚህ አገልግሎት እያዋሉ መሆኑን ሚኒስትሯ ተናግረዋል።

ከዚህም በተጨማሪም በቅርቡ ኖህ ሪል ስቴት የተባለው የግል ድርጅት የሰጠውን አፓርትመንት (የጋራ መኖሪያ ቤት) አልጋዎችና ቁሳቁሶች ተሟልተውለት ለጤና ባለሙያዎቹ አገልግሎት እንደሚውል ሚኒስትሯ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ምንም እንኳን ኢንሹራንሱ ለሁሉም ሰራተኞች ቢሆንም የቤት አሰጣጡ ግን እንደ ጤና ባለሙያዎቹ የአኗኗር ሁኔታ እንደሚወሰን ሚኒስትሯ አስረድተዋል።

አሁን ባለው መሰረት ከስድስት መቶ በላይ ለሆኑ ባለሙያዎች ቤት እንዲሰጣቸው ተለይተዋል፤ ይህም በአዲስ አበባ ሲሆን በየክልሉ ደግሞ ዩኒቨርስቲዎችም እየተዘጋጁ ነው።

ምርመራና የመለየት ሥራ
በአገሪቱ ውስጥ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 96 የደረሰ ሲሆን በአጠቃላይ የተመረመረው ሰውም ቁጥር ከስድስት ሺህ ያነሰ ነው።

የኢትዮጵያም የምርመራ ቁጥር በዓለም ትንሹ ከሚባለው ውስጥ ነው። የአለም ጤና ድርጅት በተደገጋሚ ቫይረሱ በማህበረሰቡ ዘንድ የመዛመቱን ሁኔታ ማወቅ የሚቻለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው ሲመረመር ነው በማለትም ምክሩን ለአገራት ይለግሳል።

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመቆጣጠር ትልቁና ዋነኛው ሥራ የምርመራ አቅምን መጨመር እንደሆነ የሚናገሩት የጤና ሚኒስትሯ "ከአራት አስከ አምስት ሺህ የሚሆኑ ሰዎችን በቀን ለመርመር እቅድ ያለ ሲሆን፤ ይህም በሽታው ወደ ማኅበረሰቡ ተሰራጭቷል ወይስ አልተሰራጨም የሚለውን በርግጠኝነትም ለማወቅም ያስችላል" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህም መሰረት በተለያየ የጤና ማዕከላት ላይ ያሉ የሳንባና ማንኛውም የመተንፈሻ አካላት ችግሮች ያለባቸውን፣ ማኅበረሰቡ ውስጥ ደግሞ ተጋላጭ ሊሆኑ የሚችሉ ሰዎችን የመመርመር ሥራ እንደሚጀመርም አስረድተዋል።

በቀን ያለውንም የመመርመር ሁኔታ ከማስፋት ጎን ለጎንም በአዲስ አበባም ይሁን በክልል የሚገኙ ላብራቶሪዎችንም አዲስ አበባም በየክልሉ የማስፋት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ አሁን በአዲስ አበባ ሦስት በክልሎች ደግሞ አምስት በአጠቃላይ ስምንት ላብራቶሪዎች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም እስካሁን ድረስ በሽታው ተገኘባቸው በተባሉ አካባቢዎች በአዲስ አበባ፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በባህር ዳርና አዲስ ቅዳም የሙቀት ልኬት የመስራትና ሁኔታዎችንም የመቃኘት ሥራ እየተሰራ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ተጋላጭ ናቸው ተብለው የታሰቡ 640 ሰዎች ተመርምረው ሁሉም ነፃ የሆኑ ሲሆን "በአብዛኛው በቫይረሱ የተያዙት ከውጭ የመጡ ሰዎች ናቸው። ነገር ግን በተወሰነ መልኩ የውጭ ጉዞ ታሪክ የሌላቸውም ሰዎች ላይ በሽታው ስለተገኘ ይሄንን ሰፋ አደርገን የመመርመር ሥራ እንሰራለን" ብለዋል የጤና ሚኒስትሯ ዶክትር ሊያ ታደሰ ለቢቢሲ።

source