News

3 minutes reading time (596 words)

‹‹የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸው የራሳቸውና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ደህንነት ለአደጋ ሳይጋለጥ ነው››

‹‹የህክምና ባለሙያዎች አገልግሎት የመስጠት ግዴታቸው የራሳቸውና የቅርብ ቤተሰቦቻቸው ደህንነት ለአደጋ ሳይጋለጥ ነው››

ሀኪሞች ዶት ኮም በኢትዮጽያ ህክምና ህግ ዙሪያ አዘውትሮ በመስራት ከሚታወቁት የህግ ባለሙያ አቶ ሱሌማን ሽጉጤ ጋር ሰፊ የዉይይት ቆይታ ያደረገ ሲሆን ለዛሬ በ ኮሮና ወረርሽን ዙሪያ ያደረግነውን አቅርበንላችኋል ተከታተሉት፡፡  

 በቅርቡ በጠቅላይ ሚኒስትር ቢሮ በተሰጠ መግለጫ የጤና ባለሙያዎች ለሀገራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ ተጠይቋል፤ በዚህ ጉዳይ ላይ ህክምናን የሚመለከተው ህግ ምን ይላል? ምን አስተያየት አሎት?

የአገር ደህንነት አደጋ ላይ በሚወድቅበት ጊዜ ለምሳሌ ጦርነት፣ የተፈጥሮ አደጋ ፣ ወረርሽኝ  / የህዝብን ጤንነት አደጋ ላይ የሚጥል በሽታ/ ሲከሰት …ወዘተ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ /State of emergency/ ሊታወጅ ይችላል /FDRE Constitution, Article 93/፡፡  የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን በህገመንግስቱ መሰረት የማወጅ ስልጣን ያለው የሚንስትሮች ምክር ቤት ነው፡፡መደበኛ የሆኑ መብቶች ላይም ገደብ ሊጣል ይችላል፤ ለምሳሌ የመኖር፣ የመንቀሳቀስ፣ ሀሳብን የመግለጽ መብት የመሳሰሉት፡፡ በአለም አቀፍ ደረጃም የተለያዩ ሀገራት፣ የአለም ጤና ድርጅት የበሽታው አለም አቀፍ ተስፋፊ /Pandemic/ መሆን እወጃን ተከትሎ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጀዋል፡፡

ይህንንም ተከትሎ አዋጁን ተግባራዊ በማያደርጉ ግለሰቦች ላይ የገንዘብ እና/ወይም/ የእስር ቅጣት እስከመውስድ የሚደርስ እርምጃ ሊወሰድ ይችላል፡፡ ለምሳሌ ራሺያ፣ ሳውድአረቢያ፣ አርጀንቲና፣ ዪጋንዳ፣ ሩዋንዳ….ወዘተን መጥቀስ ይቻላል፡፡ ስለዚህም የእኛም ሀገር ሌሎች ሀገራት እነደወሰኑት የአለም ጤና ድርጅትን ዲክላሬሽን ተከትሎ በተመሳሳይ ሂደት ውሳኔውን አስተላልፏል፡፡ ከዚህ ቀጥሎ ያለውን ውሳኔ መንግሰት ባለ ድርሻ አካላትን(የጤናው ዘርፍ መሪዎችን እና ባለሙያዎችን) አሳትፎ እንደ ሀገር ያለንን ቁመና በማገናዘብ ሊወስን ይገባል፡፡ የሙያውን ጸባይ ግምት ውስጥ ሳያስገቡ ተዘጋጁ ብቻ ማለት አይጠቅምም፡፡

ስለዚህ በህጉ መሰረት ማንኛውም ሰው ሀገራዊ ጥሪ/call of duty/ ሲደረግ የመሳተፍ ግዴታ አለበት፡፡  የጤና ባለሙያም አገልግሎቱን ያለበቂ ምክንያት አልሰጥም ማለት አይችልም / Refusal to provide medical assistance/service in cases of serious need- Article 537/:: የጤና ባለሙያው ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎች እየተሸሻሉ ካልሄዱ፣ ሌሎች ሰዎችም እርዳታ እንዲሰጡ ይገደዳሉ፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ ሀገሮች የጦር ሰራዊቶቻቸውን ለግዳጅ እንዳሰማሩት ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ሀገራዊ ጥሪ ሲታወጅ እንዴት ባደርገው ይሻላል የሚለውን በምክክር ቢሆን ይመረጣል፡፡


የጤና ባለሙያዎች መብት  በቂ የህክምና ግብአቶችን በተለይም Personal Protective Equipment (PPE) ሳይሟሉ አገልግሎት መስጠትን ከህግ አንጻር እንዴት ይታያል?

በመሰረቱ ማንኛወም ባለሙያ የራሱን ህይወት ለአደጋ አጋልጦ አገልግሎት ይስጥ የሚል ህግ የለም፡፡ የራሱንና ቅርብ ቤተሰቡን ህይወት ለአደጋ ሳያጋልጥ፤ ሌሎችን መርዳት በሚችልበት ሁኔታ፤ አገልግሎት የመስጠት ግዴታ፤ እንኳን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ፣ በማንኛውም ወቅት የሚጠበቅ ነው፡፡የባለሙያውን ህይወት አደጋ ላይ የማይጥሉ የተወሰኑ አነስተኛ ሪስኮች ልትወስድ ትችላለህ፡፡ በዚህ በኮሮና ወረርሽኝ ግን የበርካታ ጤና ባለሙያዎች ህይወት አደጋ ውስጥ እንዳለ በሽታው ከተዛመተባቸው ሀገሮች በተለይም ከጣልያን መረዳት እንችላለን፡፡ ይሄም PPE ከሌለ ኮሮና እንኳን ለማህበረሰቡ ለጤና ባለሙያዎችም እንደማይመለስ ማሳያ ነው፡፡ ስለዚህ ባለሙያው ህይወቱን ለመጠበቅ የሚስፈልገው ነገር ሁሉ ሊደረግለት ይገባል፡፡

ነገር ግን ባለሙያውም ምክንያታዊ እና ሚዛናዊ ሆኖ ፣ የሀገሪቱን ቁመና ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ሁሉም ነገር እስከ ጥግ ካልተሟላልኝ አልሰራም ማለት የለበትም፡፡ በቅርቡ መንግስት ኮሮናን ለመከላከል እና ለማከም በጀት እንደመደበ ሰምተናል፤ ከዚህም ውስጥ የተወሰነው ለPPE አንዲሆን መታሰብ አለበት፡፡


ጤና ባለሙያው ይህ ባልተሟላበት ሁኔታ ምን ማድረግ ይችላል?

ራስን ለከባድ አደጋ አጋልጦ መስራት አለበት የሚል ግዴታ ባይኖርም፣አደጋ የሚቀንሱ ነገሮችን እየተገበረ ስራውን እነዲቀጥል በህጉ ይጠበቅበታል፡፡ ለምሳሌ አካለዊ ቅርርብን የሚቀንሱ ቴክኖሎጂዎችን በመተግበር፤ የሚቻል ከሆነም ዲስኢንፍክት እደረጉ ደጋግሞ መጠቀም፤ የመሳሰሉትን አማራጮች አሟጦ መጠቀም ይጠበቅበታል፡፡

የጤና ባለሙያዎችም መንግስትና ህዝብ ላይ፣ የጤና ስርአቱ እንዲሻሻል ተገቢውን ግፊትና ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል፡፡ ኮሮና እንደሌላው በሽታ ባለስልጣናት ወደ ውጪ ሄደው የሚታከሙበት አይደልም፣ ህክምናው በሀገር ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ይሄም ባለስልጣናትበሀገራቸው የህክምናውን ስርአት በበቂ ሁኔታ ያለመኖሩ ቁጭት እንዲፈጥርባቸው አድርጓል፡፡ ለምሳሌ አንዳንድ የአፍረካ ሀገራት የካቢኔ አባላት በኮሮና ተይዘውባቸዋል፣ ይሄም በሀገር ውስጥ የመታከምን ችግር እንዲረዱት እያደረጋቸው ነው፡፡

በመጨረሻም ሊያስተላልፉት የሚፈልጉት መልእክት ካለዎት?

የኮሮናን አደገኛነት መንግስትም ሆነ ማህበረሰቡ በበቂ ሁኔታ የተረዱት አይመስለኝም፡፡ መንግስት አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ ደረጃ ብዙ ይቀረዋል፡፡ በቂ የላብራቶሪ ምርመራዎች እየተሰሩ አይደለም፤ ኳራንታይንም ላይ ክፍተቶች አሉ፡፡ ህዝቡም ማህበራዊ መራራቅን ተግባራው ሲያደርጉ እያየሁ አይደለም፡፡

የጤና ባለሙያው ምንም እንኳን ብሶት ቢኖርበትም፣ በዚህ ጊዜ በርታ፣ ጎበዝ እያለ ያስተማረውን ማህበረሰብ እያሰበ ግዴታውን ሊወጣ ይገባል ብዬ አስባለሁ፡፡

እናመሰግናለን፡፡

(ሀኪሞች ዶት ኮም በ ህክምና ህጎች/ Medico-legal issues/ ዙሪያ ከ አቶ ሱሌማን ጋር በሰፊው ያደረገውን ቆይታ በቅርቡ ይዘን እንቀርባለን)

My last 16 Hours in Primary Hospital. (Dr Rodas Te...
Corona Update live
 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Monday, 28 September 2020

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/