Featured articles

News

6 minutes reading time (1103 words)

''መሪነት ማለት የአንድ ሰው ህይወት የተሻለ እንዲሆን፣ በበጎ ጎን ትንሽዬ ተጽእኖ ማድረግ ነው''

2

 ሀኪሞች ዶት ኮም የአእምሮ ሀኪም ከሆነው ከ ዶ/ር ዮናስ ላቀው ጋር በአእምሮ ህክምናና በቅረብ ባሳተመው አዲስ መጽሀፍ ዙሪያ ቃለምልልስ አድርጓል፡፡ ቃለምልልሱን ሎዛ አድማሱ(4ኛ አመት የህክምና ተማሪ) እንደሚከተለው አዘጋጅታ አቅርባልናለች፣ ተከታተሉት፡፡

ሀኪሞች፡- ዶክተር ዮናስ ራስህን አስተዋውቀን፡፡

ዶክተር ዮናስ፡- ዮናስ 32 አመቱ ነው፡፡ ባለ ትዳር ነው፡፡ አማኑኤል ሆስፒታል የሚሰራ ሳይካትሪስት ነው፡፡ በትርፍ ጊዜዬ ኮሜዲ እወዳለሁ፤ አሁን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ሲኒማቶግራፊ ጀምሬአለሁ፡፡ከዚያ በተጨማሪ ፕሮፌሽናል የአዕምሮ ጤና አድቮኬት ነኝ፡፡ ፌስቡክ ላይ "Mental wellness-የአእምሮ ጤና" የሚልገጽ ላይ እጽፋለሁ፡፡ ሰዎች ለሚያነሷቸው ጥያቄዎች ምላሽ እሰጣለሁ፡፡ ህክምና ማግኘት የሚፈልጉ ሰዎችን ህክምና እሰጣለሁ፡፡

ሀኪሞች፡-በሳይካትሪ ስፔሻላይዝ እንድታደርግ ምን አነሳሳህ?

ዶክተር ዮናስ፡- ‹‹Psychiatry has a lot of rooms for philosophical speculations.›› ሳይካትሪ መማር እንደምፈልግ ልክ ገና እንደተማርን ነው ያወቅሁት ፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የሰርጀሪም ዝንባሌው ነበረኝ፡፡ GP ሆኜ ሁለቱንም ነበር የማነበው፡፡ ከጊዜያት በኋላ ለሳይካትሪ ያለኝ ዝንባሌ ይበልጥ እየጨመረ ሲመጣ፣ወሰንኩኝ፡፡

ሀኪሞች፡- ኢትዮጲያ ውስጥ በአእምሮ ጤና ላይ በመስራት ላይ የሚያጋጥሙተግዳሮቶች ደግሞም ጥሩ እድሎች ምንድን ናቸው ብለህታስባለህ?

ዶክተር ዮናስ፡- ሳይካትሪ በጣም ደስ ይላል፡፡ ሳይኮሎጂካል ዝንባሌ ያለው ሳይካትሪስት ነኝ፡፡ እኛ ሀገር እየተሰራ ያለው ሳይካትሪ ‹‹ባዮሎጂካል ሳይካትሪ›› ነው፡፡ ስለዚህ ሰዎች አሁንም የአእምሮ በሽታ የሚመስላቸው 2% የሚሆኑ ጥቂቶች፣ከባድ ህማም ያለባቸውን ነው፡፡ መንገድ ላይ ልብስ አውልቆ የሚሄድ ለብቻው የሚያወራን ነው እንደ እእምሮ ህመም እያዩ ያሉት፡፡ከዚያ በተረፈ ግን ልክ እንደ እኔና እንደ አንቺ ሸሚዝ ለብሶ፣ ኮንዶሚኒየም ቤት ውስጥ እየኖረ ያለ ሰው የአእምሮ ህመም እንደሚያጋጥመው እየታየ አይደለም፡፡ ይህ ግንዛቤ ቢኖር ጥሩ ነው፡፡ ከዚያ ደግሞ የተሻለ የንግግር የስነ-ልቦና ህክምና ቢኖር ጥሩ ነው፡፡

ተግዳሮት ከተባለ ሀላፊነቱን የሚወስዱ አካላት ብዙ ናቸው፡፡ አሁንም ሰዎች ረጅም ርቀት ተጉዘው ነው የአእምሮ ህክምና የሚያገኙት፡፡ በጣም ብዙ ገንዘብ ያወጣሉ፡፡ በአቅራቢያው፣ በየቦታው መኖር ነበረበት፡፡ የአገልግሎት ጥራቱም ያን ያህል አይደለም፡፡

ሀኪሞች፡- ምን ጥሩ እድሎች አሉት?

ዶክተር ዮናስ፡- ጥሩ አጋጣሚ ሊሆን የሚችለው ያልተሰራበት መሆኑ ነው፡፡ እነኚህን ችግሮች ለመጋፈጥ አዳዲስ መንገዶች መቀየስ እንችላለን፡፡ ይሄ ጥሩ እድል ይመስለኛል፡፡ ብዙ የሚሰራ ስራ ስላለ ጥሩ ዕድል ይመስለኛል፡፡

ሀኪሞች፡- እንደ ባለሙያ ምን ትመክራለህ፣ የአእምሮ ጤና ዘርፍን ለማሻሻል?

ዶክተር ዮናስ፡- መጀመርያ መንግስት ትልቅ ሚና ይጫወታል፡፡ በቅድሚያ የህክምና አገልግሎቱን ተደራሽ ማድረግ፣ ከዚያም ጥራቱ እንዲጨምር መደረግ አለበት፡፡ ይሄ የፖለቲካ ቁርጠኝነት ይጠይቃል፡፡ አሁን የጤና በጀቱ ሲታይ በጣም ትንሽ ነው፡፡ ከችግሩ ስፋትና ክብደት ጋር አይመጣጠንም፡፡

ከዚያ በኋላ ደግሞ ግንዛቤ ማስጨበጥ ያስፈልጋል፡፡ በአንዳንድ ሆስፒታሎች አሁን በብዙ ግፊት አልጋ እንዲኖር ተደርጓል፡፡ ሆኖም ሰዎች አገልግሎቱን ለማግኘት አይመጡም፡፡ ምክንያቱም እንዳለ አያውቁም፡፡ ተደራሽነቱን በሚገባ ካረጋገጥን በኋላ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ መስራት /advocacy/ ያስፈልጋል፡፡

በዚህ የግንዛቤ ማስጨበጫ ላይ ባለሙያዎች የራሳችን ሚና ይኖረናል /professional advocacy/፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ ታካሚዎች እና የታካሚ ቤተሰቦች ከፍተኛ ሚና ሊኖራቸው ይገባል/ Patients advocacy /፡፡ የአእምሮ ህክምና ጥራቱን የጠበቀ እንዲሆን ግንዛቤ ማስጨበጥ አለባቸው፡፡ ከዚያ በላይ ደግሞ እነሱ ይበልጥ ተሰሚነትም አላቸው፡፡ ለምሳሌ አንድ እናት ‹‹ልጄ በአማኑኤል ሆስፒታል ታክሞ በጣም ተሸሎት ወደ ትምህርት ተመልሷል››ከምትል እና እኔ ‹‹የአእምሮ ጤና ያስፈልጋል›› ከምል የእሷ ይበልጥ ተሰሚነት አለው፡፡ ሰለዚህ እዚህ ላይ መስራት ያስፈልጋል፡፡

ሀኪሞች፡- ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ለምን ትጽፋለህ? ማሳካት የምትፈልገው ግብ አለ?

ዶክተር ዮናስ፡- ማሳካት የምፈልገው ግብ አለ፡፡ ፌስቡክ ላይ መጻፍ የጀመርኩበት ምክንያት፤ የአእምሮ ህመም ሳይታከም ለረጅም ጊዜ ሲቆይ ከህክምናው ጥሩ ውጤት ስለማይገኝ ፡፡ ከዚያ ባሻገር ደግሞ በየቦታው፣አፈ-ታሪኮች/Myths/ አሉ፡፡ ለምሳሌ አሁን ‹‹የአእምሮ መድኃኒት ያጀዝባል››፤ ‹‹አማኑኤል የሚሰሩ ሀኪሞች ራሳቸው የአእምሮ ህመምተኞች ናቸው›› ሲባል ሰምተሽ ታውቂያለሽ፡፡ እነዚህ በጣም ከፍ ያለ ድምጽ እያወጡ ያሉ ቢሆኑም ጥቂቶች ናቸው፡፡ ስለዚህ አጠቃላይ እውነታውን አያሳዩም፡፡ ለምሳሌ የአእምሮ ሀኪም እንደማንኛውም ሰው የአእምሮ ህመም ሊይዘው ይችላል፡፡ ግን ሁሉም ሰው እዚያ ያለው የአእምሮ ህመም አለበት ማለት አይደለም፡፡ የአእምሮ መድሃኒት የሚወስዱ የተወሰኑ ሰዎች ላይ የጎንዮሽ ጉዳት ሊያጋጥማቸው ይችላል፡፡ ግን ሰምተናቸው የማናውቃቸው ያልተነገሩ ብዙ እውነታዎች ደግሞ አሉ /The silent majorities/፡፡ ለምሳሌ ‹‹የአእምሮ መድሃኒት ወስዶ ትምህርቱን እንዲያውም በጥሩ ውጤት አጠናቀቀ›› ሲባል ሰምተሸ ታውቂያለሽ? እንደዚህ ያሉ ነገሮች ዘወትር ይከሰታሉ ግን ምንም አይወራላቸውም፡፡ ለምሳሌ ‹‹አማኑኤል የሚሰራ ሀኪም በጣም የተረጋጋ /Balanced/ የሆነ ህይወት አለውና እንዲያውም የአእምሮ ሀኪም መሆኑ ሳይጠቅመው አይቀርም›› ሲባል ሰምተን አናውቅም፡፡

ለማንኛውም የአእምሮ ህክምናን በተመለከተ ቁጭ ብለን ሰዎች እስኪመጡ መጠበቅ በጣም አሳዛኝ ነው፡፡ ታካሚዎች ሶስት አመት፣አራት አመት፣ሀያ አመት ቆይተው ይመጣሉ፡፡ ከዚያ በኋላ ከህክምናው የሚያገኙት ጥቅም ያን ያህል አይደለም፡፡ እናም በእነዚህ ላይ ግንዛቤ ለመፍጠር ትኩረት አድርጌ ነው የምጽፈው፡፡


ሀኪሞች፡- እስኪ ስለ አዲሱ መጽሐፍህ ንገረን፡፡

ዶክተር ዮናስ፡- መፅሐፌ ‹‹ቀላሉን ነገር አታካብድ››ይላል፡፡የትርጉም ስራ ነው፡፡የዶክተር ሪቻርድ ካርልሰን ‹‹Don't sweat the small stuff…››የሚል መጽሀፍ ነው፡፡ እንዴት ልተረጉመው እንደቻልሁ የመጽሐፉ መግቢያ ላይ አለ፡፡

የሁለተኛ አመት ሬዚደንት እያለሁ ለፈተና ሁለት ሳምንት ቀርቶን ፣በጣም የሚያጨናንቅ ጊዜ ነበር፣የሆነ ሰው ድንገት የሆነ መጽሐፍ እኛ ጋር ጥሎ ይሄዳል፡፡ ጥቁር አንበሳ ከጓደኞቼ ጋር ተሰብስበን እያነበብን ነበር፡፡ ሰዎች ይመጣሉ፣ይሄዳሉ፣ ብቻ የሆነ ሰው የሆነ መጽሐፍ ጥሎ ይሄዳል፡፡ ከዚያ በኋላ በጥናት መካከል እረፍት ለመውሰድ መጽሐፉን አነሳሁት፡፡ እና እንደ አንድ ሁለት ምዕራፍ አንብቤ ድጋሚ ወደ ጥናቴ ለመመለስ ነበር ያሰብኩት፡፡ እናም መጽሐፉ በጣም መሳጭ ነበርና ቀጠልኩኝ፡፡ሶስት… አራት፣…ስድስተኛ ምዕራፍ አካባቢ ስደርስ ነው የታወቀኝ፡፡ እና ነጥቡ ቀላል ነገሮችን ማካበድ፣አንደኛ ውጤታማነታችንን ይቀንሳል፤ሁለተኛ ከፍተኛ የሆነ ጭንቀት፣የአእምሮ ጉልበትን ይወስዳል፡፡ መጽሐፉ ስለእነዚህ ጉዳዮች ይተነትናል፡፡እናም ልክ ሁለተኛው ሳምንት ሲያልቅና ፈተናው ሲደርስ አካባቢ፣ፈታ ያልኩ ሰው ሆኜ ነበር፡፡የተወሰነ እያጠናሁ፤ይሄንን መጽሐፍ ደግሞ ብዙ እያነበብኩ ነበር፡፡

ከዚያ በኋላልተረጉመው ጀመርኩትና ብዙአልገፋሁበትም፡፡አሁን በቅርቡ ድጋሚ ጊዜ ሳገኝ ይሄን ነገር መተርጎም አለብኝ ብዬ፣ጊዜ ሰጥቼው ተረጎምኩት ማለት ነው፡፡ እንዴት ጥቃቅን ነገሮች ህይወታችንን እንዳይቆጣጠሩት ማድረግ ይቻላል፤በአጭሩ መጽሐፉ ይሄ ነው፡፡ እንደ ሳይካትሪስት ከብዙ Psychotherapy schools የተወሰደ ነው፡፡ በዋናነት ደግሞ ከምስራቅ ፍልስፍናዎች ጋርም "Blend'' ተደርጓል፡፡

አብዛኛውንጊዜ ደስተኛ ለመሆን እንሯሯጣለን፤ወይንም ደግሞ ደስተኝነታችንን ለሌላ ቀን እናራዝማለን፡፡ በጣም እንለፋለን፣እንጨነቃለን፡፡ ግን ህይወት ማለት ራሱ ሂደቱ ነው፡፡ ስለዚህ ሂደቱን ልንደሰትበት ይገባል፡፡እና ይሄንን Practical በሆነ መንገድ የሚያሳዩ ዘዴዎች ናቸው መጽሐፉ ውስጥ የተካተቱት፡፡

ሀኪሞች፡- በ Young African Leaders Initiative/YALI/ የነበረህ ቆይታ እንዴት ነበር?

ዶክተር ዮናስ፡- YALI ባለፈው ሰኔ ላይ Rutgers University, New Jersey ነበር የሄድኩት፡፡ በጣም አሪፍ ነበር፡፡ በጣም የተደራጁ/organized/ ናቸው፡፡ በጣም ሰዎችን ለመርዳት ይፈልጋሉ፡፡ቆንጆ ስልጠናና በጣም አሪፍ ልምድ ነበር፡፡ በአእምሮ ጤና ላይ ከሚሰሩ ሰዎች ጋር የመገናኘት እድል ነበረኝ፡፡ተመሳሳይ ነገር የሚሰሩ ሀኪሞች ነበሩ ከተለያዩ አፍሪካ ሀገራት የመጡ ፡፡

ሀኪሞች፡- መሪነት/ Leadership/ለአንተ ምንድን ነው?

ዶክተር ዮናስ፡-መሪነት ማለት የአንድ ሰው ህይወት የተሻለ እንዲሆን፣ለበጎ ነገር ትንሽዬ ተጽእኖ ማድረግ ነው፡፡

ሀኪሞች፡- ሀኪሞች እንዴት ህክምናው ላይ ማየት የሚፈልጉትን ነገር ማምጣት ይችላሉ? እንዴት መሪዎች መሆን ይችላሉ?

ዶክተር ዮናስ፡- ትንሽዬ ተጽእኖ ማድረግ ነው፡፡ትንሽዬ ተጽእኖ ታካሚዎቻችን ላይ፣ትንሽዬ ተጽእኖ በኬዝ ቲማችን ላይ፣የሆስፒታሉ አስተዳደር ላይ፣እንዲሁም ትንሽዬ ተጽእኖ የጤና ጥበቃ ላይ እያሉ መሄድ ነው፡፡

ሀኪሞች፡- የምታስተላልፈው መልዕክት ካለ፤ ሳይካትሪ መማር ለሚፈልጉ፣መጻህፍትን መጻፍ ለሚፈልጉ

ዶክተር ዮናስ፡- መማር የሚፈልጉ ሰዎች እንግዲህ፣ ግቡ፤ ትወዱታላችሁ፡፡ በጣም ፍላጎት ከሌላችሁ ግን አትግቡ፡፡ መጻህፍትን መጻፍ ለሚፈልጉ ደግሞ፣ሁሉም ሰው መፅሐፍ አለው ውስጡ፤ያው ተጽፏል ወይስ አልተጻፈም ነው እንጂ፡፡በጣም የሚወዱትን ነገር/passionate/ መፃፍ ነው፣ እነደዛ ሲሆን ተፈጥሯዊ ይሆናል፡፡ ስለምትወጂው ነገር፣ፍላጎት ስላሳደረብሽ ነገር ስትጽፊ ሸክም አይሆንም፡፡ ሌላው "writers' cramp'' የሚባል ነገር አለ፡፡ ልትጽፊ ስትይ፣ አእምሮሽ ላይ የሚይዝ ነገር አለ፤ይሄን ማለፍ አለብን፡፡ ማንኛውም ጸሀፊ ወይም የአርት ስራ የሚሰራ ሰው የሚሰማው ነገር አለ፡፡ ማንኛውም አርቲስት የሆነ ስራ ሰርቶ ከጨረሰ በኋላ ተመልሶ ሲያየው ያስጠላዋል፡፡ የሆነ ጽሁፍ በሰዐቱ አንቺ አሪፍ ነው ብለሽ ትጽፊና ተመልሰሽ ስታይው ያናድሻል፡፡ ሲያናድድሽ ግን ተስፋመቁረጥ የለብሽም፤አሁንምመቀጠል ነው፡፡ ነገ ላይ በምትሆኚው አንቺ፣ ሲታይ ጥሩ ነገር ላይሆን ይችላል ግን የግድ መጻፍ አለበት፡፡ መፃፍ ለሚፈልጉ ሰዎች፣ ምክሬ Absurd ሊመስል ይችላል ግን Write when you feel like it… write when you don't & write more! After all, it is about getting it written is not about getting it right!

ሀኪሞች፡- ሌላ መልዕክት ካለህ እድሉን ልስጥህ

ዶክተር ዮናስ፡- መፅሀፉን ‹‹ቀላሉን ነገር አታካብድ›› ትወዱታላችሁ እናም በጃፋር መፃህፍት መደብር ታገኙታላችሁ፡፡

ሀኪሞች፡- ስለነበረን ቆይታ በሀኪሞች ዶት ኮም ተከታታዮች ስም እናመሰግናለን፡፡ 

ኮሮና ቫይረስ የአእምሮ መቃወስን እያስከተለ ነው ተባለ::
Dr. Tegbar Yigzaw is the new President of Ethiopia...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Sunday, 16 January 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/