Featured articles

News

11 minutes reading time (2199 words)

የሀገራችን የትምህርትና የጤና ተቋማት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው

የሀገራችን የትምህርትና የጤና ተቋማት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው" ትልቁ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አነጋጋሪ ነገር የደሞዝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ሳታሟላ ሌላ ሀሳብን ብታነሳ፣ ጠቃሚ ነገር እንኳን ቢሆን፣ትርጉም ባለው ሁኔታ የሰውን ህይወት አትለውጠውም፡፡ .....ይሄንን ራሱ እውቅና በመስጠት ያለምንም ወጪ በፖሊሲ ብቻ ማስተካከል ትችላለህ፡፡ "

 ዶ/ር ተግባር መጀመሪያ ዲግሪውን በህክምና ከጅማ ዩኒቨርሲቲ፣ሁለተኛ ዲግሪውን በማስተርስ ኦፍ ፐብሊክ ኸልዝ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣በኔዘርላንድ አምስተርዳም ብራይ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ ፒ.ኤች.ዲውን በፐብሊክ ኸልዝ፣ ሂውማን ሪሶርስ ፎር ኸልዝን ትኩረት አድርጎ ሰርቷል፡፡በተጨማሪም በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲ በፌመር/Faimer/ ኢንስቲትዩት በሜዲካል ኢድዩኬሽን፣ ሊደርሽፕ እና ኤዱኬሽን ሪሰርች ፌሎውሺፑን ሰርቷል፡፡በጃፓይጎ ኢትዮጲያ "Technical director and deputy chief of party, USAID's Strengthening Human resources for health project,Jhpiego" በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡እንዲሁም በጅማ ዩኒቨርሲቲ ማስተርስ ኦፍ ሜዲካል ኤዱኬሽን እያስተማረና በሌሎችም ሀገር አቀፍ ተቋማት ውስጥ በማማከር እየሰራ ይገኛል፡፡ ሀኪሞች ዶት ኮም ከ ዶ/ር ተግባር ይግዛው ጋር በሀገራችን የትምህርትና የጤና ተቋማት ተግዳሮቶችና መፍትሄዎቻቸው ዙሪያ ውይይት  አድርገጓል፡፡ ቃለምልልሱን           ዶ/ር ሳሙኤል ጌትነት እንደሚከተለው አዘጋጅቶ አቅርቦልናል፣ ተከታተሉት፡፡

ሀኪሞች፡- ዶ/ር ተግባርን እንደግለሰብ ማን ነው? እራስህን እንዴት ትገልጸዋለህ?

ዶ/ር ተግባር፡- ባለትዳር እና የ9 ዓመት ሴትና የ7ዓመት ወንድ ልጆች አባት ነኝ፡፡ ተግባር መዝናናትን የሚወድ፣ ለቤተሰቦቹ ለጓደኞቹ ለሀገሩ እና ለባህሉ ከፍተኛ ስፍራ የሚሰጥ ሰው ነው፡፡ በምሰራው ስራ ላይ በጣም ቁምነገረኛ/serious/ ነኝ፣ ስራዬን በከፍተኛ ተነሳሽነት በመስራትና ውጤት በማምጣት የማምን ሰው ነኝ፡፡ እንደግለሰብና እንደባለሙያ ትልቁ እሴት ብዬ የምቆጥረው ልህቀትን/excellence/ ነው፡፡ መካከለኛነትን አልወድም፤ ሁልጊዜ ከፍተኛውንና የተሻለውን ነገር ማድረግ፣ መስራትና ማወቅ እፈልጋለሁ፡፡ ይሄንን ለራሴ ብቻ ሳይሆን አብረውኝ ለሚሰሩ ሰዎች ሁሉ እፈልጋለሁ፡፡ ይሄም ጠንክሮ በመስራት የሚመጣ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ሂደት እንጂ በአንድ ቀን የሚመጣ ነገር አይደለም፡፡ ነገሮችን በአጭር መንገድ ከመስራት፣ ትንሽ አንብቦ፣ አስቦ የሌሎችን ሀሳብ ጠይቆ የተወሰነ ርቀት ተጉዞ በመስራት አምናለሁ፡፡ ስለዚህ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሌላ እሴቴ ነው ብዬ ማስበው መማርን ነው፡፡ ስራዎቼ መማሪያ አጋጣሚዎቼም ናቸው፡፡ ሌክቸር መስጠት፣ ፓናሊስት መሆን፣ አርቲክል መጻፍ፣ ሪፖርት መጻፍ እነዚህ ሁሉ ለመማር አጋጣሚዎቼ ናቸው፡፡ ለኔ ልህቀት የሚገለጠው ቀጣይነት ባለው የትምህርት ፍላጎት ነው፡፡ ሌላው እንደእሴት ልህቀትን፣ ጠንካራ ስራን፣ መማርን እንዳነሳሁት መዝናናትም አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ምክንያቱም ህይወት ውስጥ የምታደርጋቸውን ነገሮች የምታደርገው ደስታንና እርካታን ለማግኘት ነው፡፡ ስለዚህ ይህንን ለማድረግ ሀገር ውስጥም ከሀገር ውጪም ጉዞ አደርጋለሁ፤ በሀገር ውስጥ ያሉ ሀይማኖታዊ ባህሎችን ለምሳሌ ጥምቀት፣ መስቀልንከቤተሰብ ጋር ማሳለፍ ትልቅ ዋጋ አለው፡፡ ሙዚቃን ማድመጥም፣ ከጉዋደኞቼ ጋር ቢያንስ በሳምንት አንዴ አብሮ ማሳለፍን እወዳለሁ፡፡ ነገሮችን በቀናነት መመልከት፣ ስለሁኔታው አዎንታዊውን መንገድ መምረጥን አስቀድማለሁ፡፡ይህ አንዱ እሴቴ ነው፡፡ ነገሮችን በቀና የማያዩ ሰዎችን መረዳት እቸገራለሁ፤ አሉታዊ አስተሳሰቦችን የምታስተናግድበት ችሎታ ያስፈልግሀል፡፡ ይሄ የኔ ክፍተትና ራሴን ለማሳደግ/Emotional area of development/ የማስብብት ጉዳይ ነው፡፡ ስለዚህ ቀና አስተሳስብ አንዱ የእኔ እሴት ነው፤ ብጎዳም መልካም አስቦ መጎዳት ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀኪሞች፡- እንደባለሙያስ እራስህን እንዴት ትገልጸወለህ ?

ዶ/ር ተግባር፡- ሀኪም ነኝ፤ የህብረተሰብ ጤና ባለሙያ ስፔሻልሲት ነኝ፤ የሜዲካል ኢዱዩኬሽን ስፔሻልስት ነኝ፤ አጠቃላይ የኸልዝ ወርክ ፎርስ በተለይም የማንጅመንቱንና የሞቲቬሽን ሳይዱ ስፔሻሊስት ነኝ ብዬ አስባለሁ፡፡ በእነዚህ ሁሉ መስኮች ውስጥ አለሁበት፡፡ ነገርግን በዋናነት ትኩረት ለመስጠት፣ኸለዝ ፕሮፌሽን ላይ በማስተማር ወይንም ኸለዝ ወርክ ፎርስ ላይ መስራትን በሀገር ውስጥም በአለም አቀፍ ደረጃ አስተዋጽኦ ማድረግ የሙያዬ ዋና ግብ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ አስተዋጾው በማስተማር፣ በመምከር፣ ሪስርች በመስራትና  በማነቃቃት  እና በመምራት ሊሆን ይችላል፡፡ 

Be friend with Dr.Tegbar @ Hakimoch!


ሀኪሞች፡-   የሀገራችንን የትምህረት እና የጤና ስርአት እንዴት ትገመግመዋለህ ?

ዶ/ር ተግባር፡- ስላለው እድል ስናነሳ እኛ ከነበርንበት ጊዜ በተሻለ አሁን ብዙ የትምህርት እድሎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ዩኒቨርሲቲዎች አሉ፡፡ በተለይም መማርን ለሚፈልግ ሰው ኢንተርኔት ባለበት ዘመን እውቀት ማግኘት እንደበፊቱ አይቸገርም፣ ይህ ትልቅ እድል ነው፡፡ ነገርግን ኢትዮጵያው ውስጥ የባከነውን ነገር ስታስበው ያሳዝናል፡፡ አብዛኛው የጤና ባለሙያ በማስተማሩም ዘርፍ ወይንም በህክምናው ያለውን ብቃቱን ተጠቅሞ እየሰራ ነው ብዬ አላስብም፡፡ ባለሙያዎች ተነሳሽነት ኖሯቸው ቢሰሩ፤ ከአቅም በላይ ስለሆነው ነገር አያሳስበኝም፡፡በጥናት ተደግፌ ባይሆንም እያንዳንዱ ባለሙያ እንዲሁ ሳስበው ከግማሽ ያነሰ አቅሙን እየተጠቀመ እንዳለ ይሰማኛል፡፡ እያንዳንዳችን ‹‹የምንችለውን እያደረግን ነው ወይ?›› ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን፡፡ሀኪም የሚችለውን ያህል ታካሚ በቀን ያክማል ወይ? ያለውን እውቀት በሚችለው አቅም ለእነርሱ በእርግጥ ያውለዋል ወይ? የሚለው ጥያቄ አለኝ፡፡ ስለዚህ የጤና ባለሙያው ምናልባት ቅር በሚሉት በሚያሳዝኑት ሁኔታዎች ፍላጎቶቹ ቀንሰው ፤ተሳታፊ ሆኖ አይደለም የሚሰራው፡፡ይሄ ትልቅ ብክነት ነው፡፡ ነገርግን ያሉትን ቅሬታዎች ለጊዜው ትተን፤ ማድረግ የምንችለውን ማድረግን መቀጠል አለብን፤ ምክንያቱም እያወራን ያለነው ስለሰዎች ህይወት ነው፡፡ አንድ ሰው ማድረግ ከሚገባው ግማሹን ሲሰራ ማዳን የሚችለውን ሰው በዛኑ ያህል እያጣ ወይንም የህመሙን ጊዜ እያረዘመ ነው፡፡ በመንግስት ተቋማት ውስጥ በተለይ ተነሳሽነት ብቻ ሳይሆን ተጠያቂነት ስለሌለ፤ ያልሰራን የሚጠይቅ የሰራን የሚያበረታታ ስርዓት አለመኖሩ በራሱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ስለዚህ እኔም በሙያዬ ልሰራው የምችለውን ሁሉ ማድረግ አለብኝ ብዬ አምናለሁ፡፡

አሁን ከፍተኛ የትምህርት ጥራት ችግር አለ፤ ብዙዎቹ ከዲግሪው ባለፈ ሙያው የሚጠብቀውን ያህል እውቀትና ክህሎት የላቸውም፡፡ የትምህርት ስርዓቱን ለማስፋፋት በተደረገው ፍጥነት፣ ጥራት ያለውን ትምህርት ለመስጠት የሚያስችለውን ስርዓትና ግብዓት ሳናጠናክር ነው የሄድነው፤ ያም ዋጋ እያስከፈለን ነው፡፡ ስለዚህ አንድ ባለሙያ በቂ እውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር እንዲኖረው ማድረግ አለብን፤ በዚህም ረገድ አስተዋጽኦ እያደረገኩ ነው፤ ነገርግን የሚጠበቀው ውጤት ላይ ስላልደረስን ከዚህ የበለጠ ማድረግ አለብኝ ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀኪሞች፡- መፍትሄው ምንድነው ብለህ ታስባለህ ?

ዶ/ር ተግባር፡- ስለዚህ ዋናው ቁልፍ ነገር፣ ሰው ያለውን አቅም ተጠቅሞ በተነሳሽነት የሚሰራበትን ስርአት መፍጠር ነው፡፡ ይህ ብቻ ሳይሆን  የተጠያቂንነት ስርዓት መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ ይሄ የሂውማን ሪሶርስ ማኔጅመንት ጉዳይ ነው፡፡በተጨማሪም ከትምህርት ስርዓት ጥራት አንጻር፣ ባለሙያው ከትምህርት ገበታው ሲወጣ የሚጠበቅበትን እውቀት፣ ክህሎትና ስነምግባር ይዞ እንዲወጣ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ጉዳይም በታካሚዎች ዘንድ በቅሬታ እንደሚስተዋለው፣ ባለሙያው ከብቃቱ እኩል በሚባል መልኩ የተግባቦት ክህሎት ያስፈልገዋል ፡፡  ታካሚው የሚፈልገውን ነገር ሲጠይቅ ለምን ተናገርከኝ፣ ለምን ጠየከኝ በሚል የሚቆጣ ባለሙያ ይስተዋላል፣  የተግባቦት ክህሎት ላይ ክፍተት አለ፡፡ በእርግጥ ባለሙያ አስቦበት ያመጣው ጉዳይ ሳይሆን ከስር ጀምሮ የሚያስፈልገው ትምህርትና ዝግጅት በበቂ ሁኔታ ስላላገኘ ነው፡፡ ስለዚህ ባለሙያ ታጋሽ ሆኖ፣ ተቆርቋሪ ሆኖ፣ ልክ እንደራሱና እንደቤተሰቡ አድርጎ አገልግሎቱን እየሰጠ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ሙሉ ለሙሉ ማድረጉ ቢከብድም ቢያንስ በዚህ አቅጣጫ ጥረት ማድረጉ አስፈላጊ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡

ምናልባት ሶስተኛው ጠቅለል አድርጌ ላነሳ የምችለው፣ ማስረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲ እና ፕሮግራሚንግ/Evidence based policy and programming/ ነው፡፡ እኛ መረጃንና ጥናትን የሚገባውን ያህል ቦታ እየሰጠነው ነው ማለት ይከብደኛል፡ ትኩረት ቢሰጥበት ኖሮ ለዛ የሚገባውን በጀት መድቦ ለውጡን በአግባቡ በመከታተልና በዓለም አቀፍ ደረጃ ምን አዲስ ነገር አለ እያልክ በጥናትና በቁጥር ላይ በተመሰረተ መረጃ ላይ ታተኩራለህ፣ራስህን ትመዝናለህ፣ትለካለህ፡፡ ስለዚህ ‹‹አሁን ያለን መረጃ ከዓለም አቀፍ ሁኔታ ጋር ይሄዳል ወይ?፣ የተሰራው ጥናት የሚፈለገውን ውጤት አምጥቷል ወይ?›› የሚል በቂ ስርዓት የለም፡፡ ተነሳሽነቱም  የለም፡፡ ስለዚህ በሽተኛ ከሚያየው ጤና ባለሙያ ጀምሮ እስከላይኛው ፖሊሲን የሚያወጡት ሚኒስትሮች ድረስ ሁልጊዜ አንድ ነገር ሲሰራ ‹‹ Evidence ምን እንደሚል፣ ጥናቶች ይደግፉታል ወይ ብለን እንጠየቃለን ወይ? ›› በተጨማሪም ፍጹም የሆነ ነገር ስለሌለ፣ በመረጃና ጥናት የጀመርነውን ስራ እውነት ልክ መሆኑንና ውጤት እያመጣ መሆኑን የሚመዝን የጥናትና ቁጥጥር ባህሉ የለም፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሶስቱ፤የትምህርት ጥራት ማሻሻል፣ የተነሳሳሽነትና የተጠያቂነት ስርዓት እና መረጃን መሰረት ያደረገ ፖሊሲና ፕሮግራም ካሉ፣ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ተፅእኖ ይኖራቸዋል ብዬ አስባለሁ፡፡በጤና ሴክተሩም ላይ በትልቅ አቅም የሚሰራ የጤና ባለሙያ እናገኛለን ብዬ አምናለሁ፡፡

‹‹ ስለዚህ ምርጥ ሀኪም መሆን ከፈለኩ በእውቀትም በስነምግባርም የበለፀኩ መሆን አለብኝ፡፡ይሄን ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ ማለት አለበት፣ ይሄ መጨረሻ የሌለው ጉዞ ነው፡፡ስራ ከጀመረበት እስከሚያቆምበት ድረስ የሚቀጥል ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ብቻ ሁላችንም በተሰማራንበት ቦታ የተሻለውን ራሳችንን/Best version of ourselves/ መሆን አለብህ ነው ሀሳቡ::  ›› 

ሀኪሞች፡- በዚህ ጉዳይ ምን ምን ዝርዝር ስራዎች ሊሰሩ ይችላሉ ?

ዶ/ር ተግባር፡- በነዚህ ባነሳሁዋቸው ነጥቦች ውስጥ የሚሰሩ ስራዎች አሉ፡፡ነገርግን በእኛ ሀገር የሚሰሩ ስራዎች በሙሉ ልብ አይሰሩም፤ የተበታተኑ ናቸው፤ ሲስተሚክ አይደሉም፡፡ስርዓቱን ስር ነቀል በሆነ መንገድ የሚቀይሩ አይደሉም፡፡ ለምሳሌ አንድ ‹‹ፓሬቶ ፕሪንሲፕል›› የሚባል ነገር አለ፤ አንድ ችግር ብዙ ምክንያቶች ሊኖሩት ይችላሉ፡፡ 10 የሚያህል መስኤዎች ሊኖሩ ይችላሉ፣ ነገርግን አስሩም ለችግሩ እኩል አስተዋጽኦ አይኖራቸውም፡፡ምናልባትም ሁለቱን ብትፈታቸው የችግሩን 80% ልታስወግድ ትችላለህ፤ ሌሎቹ የችግሩ መንስኤ ቢሆኑም ትርጉም ባለው መንገድ መፍትሄ አያመጡም፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ሞቲቬሽን እና ሪቴንሽን ላይ የሚሰራው ነገር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ የማይካድ ምሳሌ የሚሆነው ለጤና ባለሙያ የሚከፈለው ደሞዝና ለስራ ሌላ ቦታ ሲሄድ የሚከፈለው አበል፣ እንኳን ለሌላ ሊተርፍ ለመኖር እንኳን የሚያስችል አይደለም፡፡በቃ መሠረታዊ ፍላጎቶቹን እንኳን አያሟላም፡፡ለምግብ፣ ለልብስ፣ ለመጠለያ፣ልጆቹን ለሚያስተምርበት እንኳን የሚያሟላበት አይደለም፡፡ ይሄን ሁሉም ሰው ያውቀዋል ግን ምንም ማድረግ አይቻልም ተብሎ ተትቷል፡፡ ምንም እንዳልተፈጠረ እያስመሰልን፣ ‹‹እኛ ተጎድተን ለሚቀጥለው ትውልድ የተሻለን ነገር እንፍጠር›› እልያክ ታወራለህ፡፡በመሰረቱ የሰው ፍላጎት የተገደበ አይደለም፣ በቃኝን አያውቅም ይሆናል፡፡ ለሀኪሞች ብቻ  ሳይሆን ፣ ማንኛውም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለ አንድ ሰራተኛ፣ ዝቀተኛ ደሞዙ/Minimum living wage/ መሰረታዊ ፍላጎቱን ማሟላት አለበት፡፡ ይሄ ደግም በጥናት ላይ መመስረት አለበት፡፡ ለአንድ ሰራተኛ ደሞዝ ስትከፍል፣ ክብሩን ጠብቆ ለመኖር የሚያስችለውን፣ መሰረታዊ ፍለጎቱን የሚያሟላ መሆን አለበት፡፡ ይሄን ካሟላን በሁዋላ እንደ መክፈል አቅምህ፣ እንደሰውየው የትምህርትና የችሎታ መጠን ደሞዙ ከፍ እያለ ሊሄድ ይችላል፡፡ትልቁ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አነጋጋሪ ነገር የደሞዝ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን ሳታሟላ ሌላ ሀሳብን ብታነሳ፣ ጠቃሚ ነገር እንኳን ቢሆን፣ትርጉም ባለው ሁኔታ የሰውን ህይወት አትለውጠውም፡፡ ይሄ ሁለት ጉዳት አለው፣ መጀመሪያው ብዙ ሰው ምሬት ውስጥ ነው ያለው፣ ደስተኛም ስላለሆነ የምትለውን መልካም ነገር እንኳን ለመስማት ፈቃደኛ አይደለም፡፡ ሁለተኛው ደግሞ መንግስትም በተከፈለ ልብ እንዲሰራ ያደርገዋል፤ በስራ ሰዓት ብትገኝ ባትገኝ፣ ሌላ ነገር ብተሰራ ባትሰራ የመናገር ድፍረቱን ያጣል፡፡ ምክንያቱም ያለውን ችግር ያውቁታል፡፡ ስለዚህ መክፈል ካልቻለ ቢያንስ ፖሊሲውን ማሻሻል አለበት፡፡ ለምሳሌ ሰውን በግልጽ ሁለት ስራ መስራት እንዲችል መፍቀድ፡፡ 8 ሰዓት በቀን አለ ፣ ከፈለክ 4 ሰአት ወይም 2 ሰአት መስራት ትችላለህ ግን በዚያ ሰአት በትክክል የሚጠበቅብህን ሁሉ ትሰራለህ፤ሙሉ ደሞዝ አይከፍልህም፡፡ያው የመንግስት ደሞዝ እምብዛም ለውጥ ስለሌለው፤4 ሰዓቱን ፕራይቬት ሴክተርም ይሁን መንግታዊ ባልሆነ ተቋም፣ የግልህን ድርጅትም ቢሆነ መስራት ትችላለህ ብሎ መልቀቅ፡፡ ይሄንን ራሱ እውቅና በመስጠት ያለምንም ወጪ በፖሊሲ ብቻ ማስተካከል ትችላለህ፡፡ ግን ተጠያቂነት ያለው ስርዓት ታደርገዋለህ፡፡ ወይም ሌላ አካል እንዲከፍል ታደርገዋለህ፤መድሀኒት እንኳን በእርዳታ ነው የሚመጣው፡፡ መድሀኒትን እና ተቋማትን ለመገንባት እርዳታ ስንጠይቅ ዘላቂነት /sustainability/ አያሳስበንም፡፡አቅም ከሌለ ለምንድነው ደሞዝ ላይ የሚደረገው ድጋፍ ዘላቂነት ጉዳይ የሚነሳው? ባይሆን እቅድ ይዘን፣ በ5-10አመት ውስጥ ድጋፉን እየቀነስን የመንግሰትን ድርሻ እያሳደግን መሄድ አንድ ነገር ነው፡፡ደሀ እንደሆንን ግልጽ ነው፤ሁሉንም ነገር የምንሰራው በብድር ነው፤ ይሄንን እውቅና መስጠት፤ ኸልዝ ወርክ ፎርሱን ማስተዳደር ላይ ልዩ የሚያደርገው ምንድነው?! ስለዚህ አሁን እየሰራንበት ያለነው የመጀመሪያውን ችግር ሳይሆን፣ ዘጠነኛና አስረኛ የሆኑት ላይ ነው፡፡

ስለ ባለሙያው የስራ መነሳሳት እና በስራ ላይ መቆየት/Motivation and retention/ ስናነሳ፤ ከገንዘብ ያለፈም ነው፡፡በቅርብ ባደረግነው ጥናት የሀኪሞች በስራ ቦታ የመቆየት ፍላጎታቸውን የሚወስነው፣ ከአስተዳደራዊና አመራር ጋር የተያያዘ ነው፤እዚህም ላይ እየሰራን አይደለም፡፡ አስተዳደሩና አመራሩ ሜሪት ቤዝድ፣ ፍትሀዊ፣ ቀና ድርጅታዊ ባህል /positive organizational culture/ ያለው መስሪያ ቤት አዋቅረሃል ወይ? ወይስ ፖለቲካ ብቻ ያጠላበት አመራር ነው? ስለዚህ መነሳሳት ላይ ትርጉም ባለው መልኩ ዋናዎቹን ጉዳዮች እየዳሰስን አይደለም፤ እንዲሁ ጥቃቅን ጉዳዮችን ለመድረስ እየሞከርን እንጂ፡፡

 ሀኪሞች፡-በትምህርት ስርአቱ ዙሪያስ ምን መደረግ ይኖርበታል?

ዶ/ር ተግባር፡-የትምህርት ጥራት ላይ መስራትን ለረጅም ጊዜ ሆነ ተብሎ ትተነው ነበር፡፡ ለምሳሌ፡ የህክምና ትምህርት ቤት ተቋም እንዲሁ ሆስፒታል በሌለበት፣ በቂ አቅም ያለው ላብራቶሪ በሌለበት፣ ሰርቶማሳያ በሌለበት፣ግባዓቱ ሳይሟላ፣ በቂ አስተማሪ ሳይኖረው ምን ጥሩ ውጤት ይጠበቃል? በሀገር ደረጃ የተቀመጠ መመዘኛ እንኳን የሚቆጣጠር አካል በሌለበት፣ አስተማሪዎቹ በቂ ኳሊፊኬሽን ከሌላቸው፣የትምህርት ሂደቱ ካልተገመገመና ካልተሻሻለ፣የትምህረት ጥራትን መጠበቅ ተአምር ነው፡፡

ዋናው ጥራትን ከምር መፈለግ አለብን፣ ከበድ ያለ ውሳኔን መወሰንም አለብን፡፡ አንድ ተቋም ቅድመ ሁኔታውን የማያሟላ ከሆነ በቃ አያሟላም ነው፡፡ ይሄ ብቻ ሳይሆን፣ የትምህርት ተቋም አመራር ላይም ችግር አለ፣ የጥራት ማሻሻል ባህልም ተነሳሽነቱም የለም፡፡ ማድረግ ያለብንን ነገር አናደርግም፣አንደገናም የምናደርጋት ነገር በምን መንገድ እናሻሽላት ተብሎ ጥረትም አይደርግም፡፡ ስለዚህ የአስተማሪ ብቃት ማነስ፣ የአስተማሪው ተነሳሽነት ማነስ፣ ህክምናው በሆስፒታል ውስጥ ባለ የትግበራ ቆይታው ላይ በቂ የሆነ የልምምድ ጊዜ ማነስ ይስተዋላል፡፡ ምዘና ብናደርግም በምዘና ወቅትም በሚያስፈልገው ልክ ደርሰዋል ወይም አልደረሱም ብለን አንመዝንም፡፡ ባይደርሱ ማለፍ የለባቸውም ብለንም አንወስንም፡፡ ስለዚህ እየተሰሩ ያሉ ነገሮች እንዳሉ ሆነው ነገርግን ቁልፍ ነገሮች፣ በተለይም ጥራት ያለው የትምህርትን ስርዓት ለመፍጠር ፣ ይበልጥ በሆስፒታል ውስጥ ባለው የትግበራ የትምህርት ስርዓት ላይ ትክክለኛ መመዘኛዎችን አስቀምጠህ፣ እነዚህ መመዘኛዎች ተፈጻሚነታቸውን የሚረጋገጥበትን ስርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ትልቁን ድርሻ ይጫወታሉ ብዬ የማስበው አስተማሪዎችን ነው፤ በቁጥርም በብቃትም ያንን መመዘኛ ካላሟላ ተቋሙ መቀጠል የለበትም፡፡ በተለይም በግል ተቋሞች ላይ የሚስተዋለው ችግር ይህ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሚተዳደሩት በትርፍ ጊዜ በሚሰሩ ባለሙያዎች ነው፣ የህክምና ተቋም በትርፍ ጊዜ ሰራተኞች መተዳደር አይችልም፡፡ ስለዚህ ብዙሀኑ ባለሙያዎች ስራዬ ብለው፣ በሙሉ ጊዜያቸው የሚሰሩ አድርገህ ተጨማሪ በትርፍ ጊዜ የሚሰሩ አስፈላጊ ምሁራንን ልትጨምር ትችላለህ፡፡ስለዚህ ባጠቃላይ አስተማሪዎች ወሳኝ ናቸው፤በሆስፒታል ያለው የትግበራ ትምህርቱ ማጠናከርም ወሳኝ ነው፤ በተጨማሪ የትምህርት ጥራቱን ባህል፣ ከውስጥ ባለ አካል ብቻ ሳይሆን ከውጪ ጥራቱን የሚቆጣጠር አካል ማካተት የሚቻል ከሆነ፣ በትምህርት ሂደቱ ላይ ስር ነቀል ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡

ሀኪሞች፡- በግለሰብ ደረጃ  አንድ ሀኪም ምን ማድረግ እንችላለን?

ዶ/ር ተግባር፡-አሁን የምለውን ነገር ሁሉ ያገኘሁት ከህክምና ትምህርት ቤት ስወጣ አይደለም፣ ነገርግን በተለያዩ አጋጣሚዎችና፣ የስራ ልምድ፣ ትምህርቶች ነው፡፡ በተለይ በህክምና ትምህርት ላይ ብዙ እንድማርና ብዙ እንድሰራ የረዳኝ ባለፉት 12 ዓመታት ጃፓይጎ ውስጥ የሰራሁት ነገር ነው፡፡ በሀገር ደረጃ በካሪኩለም ዲዛይን፣ በፋኩሊቲ ዲቨሎፕመንት ፖሊሲንና ስትራቴጂ ማርቀቅ ላይ ለመሳተፍ እድሉን ስላገኘሁ ነው፡፡ ቅድም እንዳልኩት ይህ ሁሉ ለኔ መማሪያዬ ነበር፡፡

አንድ አዲስ ወጣት ምሩቅ ሀኪም ምን ሊያደርግ ይችላል ካልከኝ፣ ትልቁ ነገር ተነሳሽነት ነው ብይ ነው የማስበው፡፡ለመማርና የምችለውን ሁሉ ለማድረግ እፈልጋለሁ የሚል ተነሰሽነት፡፡ ለመማር ተነሳሽነት ስል ታኪሚ ፊት ቢሆን፣ ኦፒዲ  ሲቀመጥ፣ በሆስፒታልም ቢሆን በጤና ጣቢያ፣ በኮሌጅ ማስተማርም ቢሆን ሁሌም ራሱን ይጠይቅ፡፡ በምሰራው ስራ ውስጥ የተሻለ ነገርን ለማድረግ ምን ማድረግ አለብኝ፣ አስተማሪም ከሆነ ምርጥ አስተማሪ መሆን አለብኝ የሚል ፍላጎት ቢኖረው! ይህን ሲያስብ በራሱ ጥረት የማስተማር ክህሎት ስልጠናን መውሰድ፡፡ እንዴት አድርጌ ነው ምርጥ ሀኪም የምሆነው የሚል መሆን አለበት፡፡ምርጥ ሀኪም ማለት ታካሚውን የሚፈልገውን የሚያደርግ፣ ማለትም አክብሮ፣ ተቆርቁሮና እንደራሱ አስቦ የሚሰራ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ምርጥ ሀኪም መሆን ከፈለኩ በእውቀትም በስነምግባርም የበለፀኩ መሆን አለብኝ፡፡ይሄን ለመሆን ጥረት አደርጋለሁ ማለት አለበት፣ ይሄ መጨረሻ የሌለው ጉዞ ነው፡፡ስራ ከጀመረበት እስከሚያቆምበት ድረስ የሚቀጥል ከፍተኛ ተነሳሽነት የሚፈልግ ነገር ነው፡፡ብቻ ሁላችንም በተሰማራንበት ቦታ የተሻለውን ራሳችንን/Best version of ourselves/ መሆን አለብህ ነው ሀሳቡ:: የምትሰራው ስራ ምንም ይሁን፤ ከዛሬ ነገ ራስን ማሻሻል፣ የተሻለ ሰውም ስናይ ምሳሌ መውሰድ፣ ለመማር መፈለግ፣ ለማወቅ መፈለግ፣ ለመሻሻል መፈለግን ለሁሉም ሰው እመክራለሁ፡፡ ባለችህ ሀላፊነት ሁሌ የምትችለውን አድርግ፣ የምትችለውን ሁን ነው ምክሬ፡፡

በመጨረሻም ለአንድ ወጣት ለሆነ/ለሆነች ሀኪም ወይንም የጤና ባለሙያ መምከር የምፈልገው ነገር፣ የእውቅት መለኪያ ወይንም የስኬት መለኪያ በአንድ ሙያ ብቻ ጎበዝ መሆን ማለት አይደለም፡፡ ይህቺ በጣም አንድ፣ ኢመንት ነገር ነች፡፡እኔ እንደዛ ፍጹም ነኝ ብዬ ባላስብም፣ ሰው ሁለገብ መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ፡፡ ሀኪም መሆን የዓለም መጨረሻ አይደለም፡፡ በትምህርት ክፍልህ ሊቅ ልትሆን ትችላለህ፣ ያ ምንም ማለት አይደለም፡፡ በተለይ የጤና ስርዓቱንና የትምህርት ስርዓቱን መቀየር ስንል ከብዙ ሰዎች ጋር መስራት አለብን፡፡ የብዙ የትምህርት ክፍሎች ሀሳብና እውቀት ያስፈልገናል፡፡ ሀኪሞች በዚህ ውስጥ አንድ አስፈላጊ የሆነ ድርሻ እንዳላቸው እንዲገነዘቡና እኔ ብቻ ነኝ በጣም ጠቃሚ ብለው እንዳያስቡ ነው፡፡ ይሄ ለመማር ለማወቅ ለማደግ እድል ይነሳል፡፡ በዓለም ውስጥ በጣም ብዙ እውቀት አለ፡፡ ከባህል ህክምናው፣ ከሌሎች የጤና ባለሙያዎች፣ ከምጣኔ ሀብት ባለሙዎች፣ ከታሪክ ብዙ ልንማር እንችላለን፡፡ የዓለም ችግሮች የሚፈቱት ከራስ የትምህርት ክፍል አልፎ/Trans disciplinary/ ለመማር ክፍት በሆነ አስተሳሰብ ነው:: ህክምናው እየተቀየረ ያለው  በቴክኖሎጂውና በፊዚክዝ እገዛ ነው:: ጂኖሚክስን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል:: ከራስ ትምህርት ክፍል ባለፈ ያለውን እውቀት የመካፈል  እምቅ ኃይልን መረዳት አለባቸው፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተከባብረንና ተቀራርበን መስራት መቻል አለብን፡፡ ህክምና ብቻ ላይ ከሆንን በራሱ ያንሳል ይጠባል፤ የህይወትን ጸጋ አናየውም፡፡ነገርግን እየኖርን ያለነውን ችግር ለመፍታት ከሌሎች ሙያዎች ጋር መስራት አለብን፤ የዛ ምቾት እና መነሳሳት ሊኖረን ይገባል፡፡

ሀኪሞች፡- ስለነበረን ቆይታ በሀኪሞች ዶት ኮም ተከታታዮች ስም እናመሰግናለን፡፡ 

የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ ለአጠቃላይ ሆስፒታሉ የገንዘብና የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ...
Job for Master-level degree in Medicine, Internati...

Related Posts

 

Comments 2

Tadiwos Hailu on Friday, 21 February 2020 11:31

Thank you Dr. Tegbar for the insights!

Thank you Dr. Tegbar for the insights!
Tadiwos Hailu on Friday, 21 February 2020 11:34

Thank you for the insights.

Thank you for the insights.
Already Registered? Login Here
Guest
Sunday, 02 October 2022

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/