News

2 minutes reading time (428 words)

የሆስፒታሎች ቆሻሻ አወጋገድ በህብረተሰቡ ላይ የጤና ችግር መፍጠሩ ተገለፀ

የሆስፒታሎች ቆሻሻ አወጋገድ በህብረተሰቡ ላይ የጤና ችግር መፍጠሩ ተገለፀ

አዲስ አበባ፡- የመንግስት ሆስፒታሎች ቆሻሻ አወጋገድ ስርዓት የአየር ብክለት ስለሚፈጥር በህብረተሰቡ ጤና ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሚገኝ ተገለፀ፡፡ ዘመናዊ የቆሻሻ ማቃጠያ ማሽኖች በጥገና እጥረት ምክንያት በአግባቡ እያገለገሉ አለመሆኑንም ተጠቅሷል ፡፡

በዳግማዊ ምኒልክ ሪፈራል ሆስፒታል የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት ዳይሬክተር አቶ ሸዋንግዛው ውብሸት በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናሩት፤ ሆስፒታሉ ፍሳሽና ደረቅ ቆሻሻዎችን የሚያስወግድበት ስርዓት አለው፡፡ የተበከሉና ያልተበከሉ ደረቅ ቆሻሻዎችን የሚቃጥልበት ዘመናዊ ማሽንና ከጡብ የተሰራ ስፍራ አዘጋጅቷል፡፡ ለፍሳሽ ቆሻሻዎች ደግሞ ከቀበና ወንዝ ጋር የተገናኘ መስመር ዘርግቷል፡፡

ሆስፒታሉ የደረቅም ሆነ የፍሳሽ ቆሻሻ አወጋገዱ አካባቢንና አየርን በሚበክል መልኩ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ሸዋንግዛው፤ ደረቅ ቆሻሻዎችን ለማቃጠል የተሰራው ዘመናዊ ማሽን በአግባቡ ጥገና ስለማይደረግለት አብዛኛው የማቃጠል ስራ የሚከናወነው በጡብ በተሰራው ማቃጠያ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በጡብ የተሰራው ማቃጠያ ደግሞ አየር ከመበከልም አልፎ በአካባቢው በሚኖሩት ሰዎች ላይ ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

የፍሳሽ ማስወገጃውም ቀጥታ ከቀበና ወንዝ ጋር የተገናኘ በመሆኑ የውሃ ብክለት እንደሚያስከትል ጠቅሰው፤ ችግሩን ይፈታል የተባለው 26 ሚሊዮን ብር የፈጀው የፍሳሽ ማጣሪያ ግንባታ ኮንትራክተሩ በማዘግየቱ ምክንያት ወደ ተግባር አለመግባቱን ጠቁመዋል፡፡ ከማዋለጃና ከቀዶ ጥገና ክፍል የሚወጡ ቆሻሻዎች በተዘጋጀላቸው መቅበሪያ እንደሚወገዱ አመልክተዋል፡፡

በዘውዲቱ ሆስፒታል የአካባቢ ጤና አጠባበቅ አስተባባሪና ባለሙያ አቶ ሰለሞን ረጋሳ፤ ከሆስፒታሉ የሚወጡ የተበከሉና ያልተበከሉ ቆሻሻዎች እንዳሉ በመጥቀስ፤ የተበከሉ ቆሻሻዎችን በማቃጠልና በመቅበር፤ እንዲሁም ያልተበከሉ ቆሻሻዎችን በደረቅ ቆሻሻ አንሺዎች እንዲወሰዱ እንደሚደረግ ተናግረዋል፡፡

የተበከሉ ቆሻሻዎች በጡብ በተሰራ የማቃጠያ ስፍራ እንዲቃጠሉ ቢደረግ በአካባቢው ብክለት እንደሚደርስ ጠቅሰዋል፡፡ ሆስፒታሉ በተወሰነ ደረጃ ብክለት ለመቀነስ ቆሻሻዎችን በማታው ሰዓት እንደሚያቃጥልም አስረድተዋል፡፡ የማቃጠያው ስፍራ ከአምባሳደር ፓርክ አጥር ስር የሚገኝ በመሆኑ በቀጣይ ፓርኩ ስራ ሲጀምር ቃጠሎው ስጋት እንደሚፈጥር ተናግረዋል፡፡ ሆስፒታሉ ዝቅተኛ አቅም የማቃጠያ ማሽን ቢኖረውም በአሁኑ ወቅት ተበላሽቶ የተቀመጠ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

እንደ አቶ ሰለሞን ገለጻ፤ የፍሳሽ ቆሻሻ ማስወገጃዎች በቀጥታ ከአምባሳደር ወንዝ ጋር የተያያዙ በመሆናቸው የውሃ ብክለት እያደረሱ ይገኛሉ፡፡ በሆስፒታሉ የሚገኘው ሴፍቲክ ታንክ የማጠራቀም አቅም ዝቅተኛ ነው፡፡ ፍሳሹ ከላውንደሪና ከማዋለጃ ክፍል የሚወጣ በመሆኑ በቀጥታ ወደ ወንዝ መግባቱ አደገኛ ነው፡፡

የጋንዲ መታሰቢያ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ታሪኩ ደሬሳ እንደሚናገሩት፤ የሆስፒታሉ ቆሻሻዎች የሚወገዱት በማቃጠያ ማሽን ነው፡፡ ነገር ግን፤ ማሽኑ የተተከለበት ቦታ ምቹ ባለመሆኑ ቆሻሻዎች ሲቃጠሉ መጥፎ ጠረን ይወጣል። ቆሻሻው እርጥበት ሲነካው ደግሞ ይሸታል። ለማቃጠያነት የተተከለው ማሽን ብዙ ውሃ ስለሚጠቀም በሆስፒታሉ ያለው የውሃ እጥረት ቆሻሻዎች በፍጥነት እንዳይቃጠሉ አድርጓል፡፡

ሆስፒታሉ ዘመናዊ የቆሻሻ ማቃጠያ ማሽን ያስተከለ ሲሆን፤ ማሽኑ ከ800 ዲግሪ ሼልሸስ በታች የሆኑ ቆሻሻዎችን በሙቀት እንደሚያቃጥል ገልፀዋል፡፡ ማሽኑ ከአካባቢ ጋር ተስማሚ በሆነ መልኩ ቆሻሻዎችን በአመድና በእንፋሎት መልክ እንዲወጡ የሚያደርግ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ ነገር ግን፤ ማሽኑ በየጊዜው ጥገና ስለማይደረግለት የተፈለገውን ያክል አገልግሎት እየሰጠ አለመሆኑን አብራርተዋል፡፡ የተከመሩት ቆሻሻዎች በአካባቢው ላይ ችግር እንዳይፈጥሩም ወደ ሌሎች ሆስፒታሎች ተቃጥለው እንዲወገዱ እንደሚላኩ አስረድተዋል::

በሆስፒታሉ ውስጥ ያለውን የቆሻሻ ክምር ከርጥበት ለመከላከል ቆሻሻ ማጠራቀሚያ ሼዶች እየተሰሩ መሆኑን የጠቀሱት ዶክተር ታሪኩ፤ የውሃ እጥረቱን ለመፍታት በግቢው ውስጥ የሚገኘውን የጉድጓድ ውሃ አስፈላጊውን ጥገና አድርጎ ለመጠቀም እቅድ እንዳለም አመልክተዋል፡፡ ማሽኑ በፍጥነት እንዲጠገን ከአቅራቢው ድርጅቱ ጋር መገናኘት እና ለማሽኑ የሚሆኑ ባለሙያዎች የማዘጋጀት ስራ በቀጣይ እንደሚከናወን ገልጸዋል::

አዲስ ዘመን ጥር 25/2012

source


"ሐረማያ ዩኒቨርስቲ ጤናና ህክምና ሳይንስ ኮሌጅ 1000 የሚሆኑ የምርምር ስራ...
Sucessful corneal transplant done on 3 month old i...

Related Posts

 

Comments

No comments made yet. Be the first to submit a comment
Already Registered? Login Here
Guest
Monday, 28 September 2020

By accepting you will be accessing a service provided by a third-party external to https://hakimoch.com/